በቀን ሰዎች፣ በሌሊት የዱር እንስሳት የሚራኮቱበት የሐርጌሌ ወንዝ ጨዋማው ውሃ

85

ሐርጌሌ ከተማ ከሱማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ 790 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። የአፍዴር ዞን እና የሐርጌሌ ወረዳ ዋና ከተማ ስትሆን በከተማዋ ምስራቃዊ ዳርቻ በአሸዋ የተሞላውን ወንዝ ደግሞ ሐርጌሌ ይሉታል።

ወትሮውኑም ወራጅ ውሃ የሚናፍቀው ሐርጌሌ ወንዝ አካባቢው ባጋጠመ ድርቅ ሳቢያ ውሃ ከራቀው ወራት ተቆጥረዋል።

ቀድሞ ከተማዋ አግኝታው የነበረ የውሃ አገልግሎት በድርቅ ሳቢያ በመቆሙ ነዋሪዎች ያላቸው አማራጭ የደረቀውን የሐርጌሌ ወንዝ አሸዋ መማስ ሆኗል።

የሚወጣው ውሃ ምንም ስንኳ ጨዋማ ቢሆንም ዳሩ ውሃ ጥም ጊዜ አይሰጥምና፣ ነዋሪዎቹ በጥዋቱ በወረፋ የተሰለፉ የሐርጌሌ ከተማ ነዋሪዎች በርሜል የጫኑ የአህያ ጋሪዎቻቸውን ይዘው ከወንዙ ይከትማሉ፣ የጠማቸውም ወረፋቸውን ጠብቀው ይጠጣሉ።

የወረዳው ውሃ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በሽር አብዲ ወረዳው 20 ቀበሌና 47 መንደሮች የእንስሳትና የሰው ምግብ ርዳታ እንደሚሹ ገልጸዋል።

የዞኑን ዋና ከተማ ሐርጌሌን ጨምር የተሻለ ውሃ ለማግኘት የግድ 30 ኪሎሜትር ማቋረጥ ይጠይቃል ይላሉ።

በወረዳው ሐርጌሌና ጨረቲ ከተሞችም የቀድሞው ውሃ አገልግሎት በመቋረጡ ነዋሪዎች ሌላ ውሃ ፍለጋ ከአንበሳ ጋር መራኮት ይዘዋል ብለዋል።

በሐርጌላ ወንዝም ቀን ቀን ሰዎች በወረፋ ከአሸዋ ጨዋማውን ውሃ ለማግኘት ሲኳትኑ፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ አንበሳን ጨምሮ የዱር እንስሳት ሲራኮቱ ያድራሉ።

በዚህ የሐርጌሌ ወንዝ ጨዋማ የሰውና የዱር አራዊት መራኮቻ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

ህዝቡ ለርሀብ ተጋልጧል፣ አደጋ የተጋረጠበት እንደሆነ ገልፀው፤ የሚመለከተው የፌዴራልና የክልል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የሐርጌሌ ወረዳ አስተዳደር ፉዓድ ሸህ መሀመድ እንዳሉት፣ ከሌሎች ወረዳ አንፃር የጉድጓድ ውሃ/ኤል/ የለውም።

ለዓመታት ሲያገለግል የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ ግድብ በድርቁ ሳቢያ በመቆሙ፣ የነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ዕጣ ፈንታ ጨዋማ ከሆነው አሸዋው ሐርጌሌ ወንዝ አሸዋን መማስ ሆኗል።

ከወረዳው 135 ሺህ ሰዎች ውስጥ 70 በመቶው ለውሃ ችግር መጋለጣቸውን ገልፀው፣ በሐርጌሌ ከተማ ደግሞ 30 ሺህ ሰዎች ለዚህ ችግር ተጋልጠዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም