በቦረና ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳት በድርቅ ምክንያት ለከፍተኛ የውሃ ለችግር ተዳርገዋል

230

 ጥር 16/2014(ኢዜአ) በቦረና ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳት በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ለከፍተኛ የውሃና የምግብ ችግር መዳረጋቸውን የፓርኩ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ በአካባቢው ነዋሪዎችና በተለይም በቤት እንስሳቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉ ተነግሯል።

በድርቁ ምክንያት በቦረና ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚኖሩ የዱር እንስሳት ለከፍተኛ የውሃ እና የምግብ ችግር በመዳረጋቸው ለሞትና ስደት መዳረጋቸውን የፓርኩ አስተዳደር ገልፇል።

በቦረና ብሔራዊ ፓርክ ግሬዝ ዜብራ፣ አጋዘን፣ የሜዳ አህያ፣ ሰጎን፣ ቀጭኔ እና አንበሳን ጨምሮ ሌሎች ከ286 በላይ የአእዋፋት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

በፓርኩ የኢኮ ቱሪዝም ባለሙያ የሆኑት አቶ ጉፉ ከሺና በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በድርቁ ምክንያት በርካታ የዱር እንስሳት ከፍተኛ የውሃ እና የምግብ እጦት ገጥሟቸዋል ብለዋል።

በአካባቢው በተከሰተው የከፋ ድርቅ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሜዳ አህያ፣ ከርከሮዎችና ሌሎችም መሞታቸውን ገልጸዋል።

የዱር እንስሳቱ ሞትና ስደት ፓርኩ ባሉት አምስት ክፍሎች ወይም ብሎኮች ውስጥ የሚታይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የብሔራዊ ፓርኩ እስካውት ሃላፊ እና የቢሮ ተወካይ ኦኮቱዲ ዳለኬ፤ በፓርኩ ከሚገኙት የዱር አንስሳት መካከል በተለይም ግሪዝ ዜብራ፣ አጋዘን እና ከርከሮ በድርቁ ሳቢያ ህልውናቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ብለዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ አንዳንድ አርሶ አደሮች በሞተር ታግዘው ከመሬት ወስጥ በሚያወጡበት ውሃ ለዱር እንስሳቱ ውሃ ሲሰጡ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

የፓርኩ የኢኮ ቱሪዝም ባለሙያ አቶ ጉፉ ከሺና፤ የዱር እንስሳቱ አደጋ ውስጥ በመሆናቸው መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የድርቁ ችግር በዚሁ ከቀጠለ በፓርኩ ባሉት በርካታ የዱር እንስሳት የመኖር ህልውና ላይ አደጋ ጋርጧል ብለዋል።  

የቦረና ብሔራዊ ፓርክ በ2005 ዓ.ም ህጋዊ እውቅና አግኝቶ የተቋቋመ ሲሆን 5 ክፍሎች ወይም ብሎኮች አሉት፡፡

የፓርኩ ብሎኮች ሳሪቴ፣ ዲደራ፣ ደንበላ ዲባዩ፣ ደዳ ሶዶ እና መጋዶ በመባል ይጠቀሳሉ።