ለአየር ትንበያ መረጃዎች ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን መቀነስ ይገባል

86

አዲስ አበባ፣  ጥር 16/2014(ኢዜአ) ለአየር ትንበያ መረጃዎች ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን መቀነስ እንደሚገባ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩት ያለፈውን የበጋ ወቅት ትንበያውን ከባለድርሻ አካላት ጋር የገመገመ ሲሆን፤ የቀጣዩን የበልግ ወራት ትንበያውንም ይፋ አድርጓል፡፡

የኢንስትቲዩቱ የበጋ ወራት ትንበያዎች አብዘሃኛዎቹ በመሬት ላይ የታዩ መሆናቸውም ነው የተገመገመው፡፡

የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በዚህን ወቅት እንደተናገሩት፤ ከበልግ ዝናብ ሽፋን አኳያ ደግሞ አብዛኛው የምዕራብ አጋማሽ  የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የበልግ ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በዋናነት የበልግ ዝናብ ከሚያገኙ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች 20 በመቶ ከመደበኛው በላይ፣45 በመቶ መደበኛና 36 በመቶ ከመደበኛ በታች የበልግ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉም ነው የገለጹት፡፡

የበልግ ወራት ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የአገሪቱ የሰሜን ምስራቅና መካከለኛው የሃገሪቱ ክፍል እንዲሁም የደቡብ ከፍተኛ ቦታዎችና ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የበልግ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉም እንዲሁ፡፡

ትንበያው ከጊዜ አንፃር ሲታይ ዝናቡ ዘግይቶ እንደሚመጣ የሚያሳይ ሲሆን፤ ዝናቡ ጥሩ ሁኔታ ላይ የሚደርሰው ከመጋቢት እስከ ሚያዚያ ባሉት ጊዜያት ሊሆን እንደሚችልም ነው የጠቀሱት፡፡

ከዚህ አኳያ የበልግ ዝናብ ዘግይቶ በሚጀምርባቸው አካባቢዎች ተጎጂ እንዳይሆኑ ከወዲሁ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኢንስትቲዩቱ የሚያወጣቸውን የትንበያ መረጃዎች በመተንተንና በመተርጎም ወደ ተግባር እንዲቀይሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም