የቴክኖሎጂ እውቀታችንን በማጋራት በኢትዮጵያ ልማትና እድገት ላይ አሻራችንን ለማኖር ተዘጋጅተናል

114

ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሳተፍና የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማጋራት በኢትዮጵያ እድገት ላይ አሻራቸውን ለማኖር መዘጋጀታቸውን ነዋሪነታቸው በደቡብ አፍሪካ የሆኑ ሁለት ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ባሉ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንትና የንግድ መስኮች ለመሰማራት መነሳሳታቸውን ለኢዜአ የገለጹት ዳያስፖራዎቹ፤ ለአገር እና ለወገን በሚጠቅም ዘርፍ ላይ በመሰማራት ለኢኮኖሚ ልማት አስተዋፅኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በሚኖሩበት አገር ያገኙትን ልምድና ክህሎት በመቀመር በኢትዮጵያ ለመተግበር ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ በኢትዮጵያ የልማትና እድገት እንቅስቃሴ ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

በየትኛውም ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ባለውለታ ለመሆን በሚችሉት የልማት መስክ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ፓስተር ወርቅነህ ዘርፉ የተባሉት የደቡብ አፍሪካ ዳያስፖራ አባል በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

መንግስት በኢንቨስትመንት መስኩ ያጋጥሙ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታት ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

እልፍነሽ ሃይሌ የተባሉ የደቡብ አፍሪካ ዳያስፖራ አባል በበኩላቸው “ሁሉም በየሙያው ኢትዮጵያን ለማገልገል ተዘጋጅቷል" ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን እናት አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈም ምሁራኖች በሙያቸው የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ሙሉ ፈቃደኝነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ችግር በፍጥነት እንድወጣ በተለይም ዳያስፖራው የሚኖረው ሚና እና ተሳትፎ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ የቱሪዝም መስህቦችን እና ምርቶችን በማስተዋወቅ የድርሻችንን መወጣት አለብን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም