የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ከቀናት በኋላ ወደ በረራ ሊያስገባ ነው

82

ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀናት በኋላ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ወደ በረራ ሊያስገባ መሆኑን አስታወቀ፡፡

አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹን ለድጋሚ በረራ ዝግጁ ያደረገው ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ የበረራ ተቆጣጣሪዎችና ሌሎች በርካታ የቁጥጥር አካላት የተደረገውን ተደጋጋሚ የደህንነት ማረጋገጫ ተከትሎ መሆኑንም ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

ለበረራ ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠው አየር መንገዱ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለበረራ ዝግጁ ያደረገው 36 አየር መንገዶች አውሮፕላኖቹን ለንግድ በረራ መጠቀማቸውንና ደህንነታቸው የተረጋገጠ መሆኑን ተከትሎ የወሰነው ውሳኔ እንደሆነም ጨምሮ ገልጿል፡፡

እንዲሁም 36 አየር መንገዶች ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ከ3 መቶ 30 ሺህ በላይ ተጓዦችን ሲያጓጉዙ የደህንነት ችግር እንዳልገጠማቸው አየር መንገዱ በዋቢነት ገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የአየር መንገዱ አብራሪዎች፣የበረራ መሃንዲሶች፣ የአውሮፕላን ጥገና እና የመስተንግዶ ባለሙያዎቹ በሙሉ ደህንነቱ ለተረጋገጠ በረራ ዝግጁ በመሆናቸው ጭምር የተወሰነ ውሳኔ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም