በዞኑ በበጋ መስኖ በ300 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር እየተባዛ ነው-መምሪያው

117

ደብረ ማርቆስ ጥር 15/2014 (ኢዜአ)- በምስራቅ ጎጃም ዞን በበጋ መስኖ በ300 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የመስኖ ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት  በበጋ መስኖ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ መስራች የስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት እየተከናወነ ነው።

የምርጥ ዘር ብዜቱ  በደብርማርቆስ ዩኒቨርስቲና ግብርና ምርምር በመታገዝ  በስድስት ወረዳዎች እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዘር ብዜቱ 400 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው እየለማ ካለው መሬት 13 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል ።

የዘር ብዜቱን ውጤታማ ለማድረግ ከ1 ሺህ 50 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ቅጥም ላይ መዋሉን  ተናግረዋል።

እየተባዙ ያሉት ቀቀባ፣ ሊሙና ዳካ የተባሉ የስንዴ ምርጥ ዘሮች በሄክታር ከ45 ኩንታል በላይ ምርት መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ የዘር ብዜቱ እየተካሄደ ያለው እየጨመረ የመጣውን የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሟላት ነው ።

በዘር ብዜቱ እየተሳተፉ ካሉ መካከል የማቻከል ወረዳ የግራ ቅዳማን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ልመንህ ደርጃው እንዳሉት ከአንድ ሄክታር በላይ የሚሆን ማሳ ላይ መስራች የስንዴ ዘር እያለሙ ነው።

ከዚህ በፊት በዘርፉ ተሳትፈው እንደማያውቁ የገለጹት አርሶ አደሩ ባለፉት ተከታታይ አመታት የስንዴ ዘር እጥረት ገጥሟቸው በመቸገራቸው በዘር ብዜቱ ለመሳተፍ መነሳሳታቸውን ገልፀዋል።

"በዚህ አመት በግማሽ ሄክትር ማሳ ላይ የስንዴ ዘር እያባዛሁ ነው" ያሉት ደግሞ የባሶሊበን ወረዳ የላምጌጅ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙቀትሁን ባዜ ናቸው።

በተደጋጋሚ ለሚገጥማቸው የዘር እጥረት መፍትሄ ለማበጀት በልማቱ እየተሳተፉ መሆናቸውን አርሶ አደሩ አስታውቀዋል ።

በዞኑ በመኽር ወቅት በተካሄደ የዘር ብዜት  ከ9 ሺህ 800 ኩንታል በላይ የጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላና ሽንብራ ምርጥ ዘር  መገኘቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም