ጋሸናን ወደ ቀደመ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ለመመለስ በውጭና በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ተጠየቀ

62

ጥር 16/2014/ኢዜአ/ ጋሸና ከተማን መልሶ በማቋቋም ወደ ቀደመ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ለመመለስ በውጭና በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ የከተማዋ ከንቲባ ሞላ ፀጋው ጥሪ አቀረቡ።

የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በአማራ ክልል ወረራ በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው ከተሞች መካከል ጋሸና አንዷ ናት፡፡

የጋሸና ከተማ ከንቲባ ሞላ ፀጋው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሽብር ቡድኑ በከተማዋ ከፍተኛ ሠብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል፡፡

ሠላማዊ ዜጎችን በመጨፍጨፍ፣ ሴቶችን በመድፈር እንዲሁም የኅብረተሰቡን ሀብት በማውደምና በመዝረፍ ከፍተኛ በደልና ሰቆቃ መፈፀሙንም ነው የገለጹት፡፡

የጋሸና ከተማ ነዋሪዎች በእልህና በወኔ ከተማዋን ወደ ቀደመ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ለመመለስ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ከውድመትና ዝርፊያ የተረፈውን ሃብት በማደራጀት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የሽብር ቡድኑ ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ ከተማዋን መልሶ በማቋቋም ወደ ቀደመ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ለመመለስ በውጭና በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ድጋፍ ጠይቀዋል።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት ህፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ለረሃብና ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በመድሃኒት እጥረት ጭምር ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች መኖራቸውን ገልፀዋል።

በከተማዋ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት የደረሰ በመሆኑ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መላ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ደግሞ ዳያስፖራው ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም