በዳሃና ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ20 ሰዎች ህይወት አለፈ

116

ሰቆጣ፤ ጥር 16/2014 (ኢዜአ)፡ በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በዳሃና ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ20 ሰዎች ህይወት ማለፉንና በስድስት ሰዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሲሳይ አበራው ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ትናንት ከቀኑ 10:30 አካባቢ ከአምደወርቅ ከተማ ወጣ ብሎ ነው።

አደጋው የደረሰው መነሻውን ባህር ዳር አድርጎ በአዲስ ዘመን እብናት ዳህና ወደ ሰቆጣ ይጓዝ የነበረ ታርጋ ቁጥር ኮድ 3 አ.ማ 11300 የሆነ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ መንገድ ስቶ 200 ሜትር ጥልቀት ካለው ገደል ውስጥ በመግባቱ እንደሆነ ገልጸዋል።

ተሽከርካሪው  ያሳፈረው የሰው ቁጥር መጠን ለጊዜው በውል ባይታወቅም እስካሁን በአደጋው የ20 ሰዎች ህይዎት ማለፉን ጠቅሰው፤ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል።

በአንድ ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ህፃን እስካሁን እንዳልተገኘች ጠቅሰው፤ በአደጋ ህይወታቸው ካለፉት ተሳፋሪዎች መካከል ሁለት የትዳር ጥንዶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ከሟቾች ውስጥም የመኪናው አካል የተጫነው የአንድ ተሳፋሪ አስከሬን እስካሁን ከገደሉ አልወጣም።

በአደጋውም የአንድ ዓመት ህፃን ልጅን ጨምሮ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ስድስት ሰዎች  በአምደወርቅና በሰቆጣ ተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ገልጸው፤ አደጋው በመንገዱ አስቸጋሪነትና በአሽከርካሪው ፍጥነት የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ብለዋል።

አሽከርካሪዎች የፍጥነት ወሰንን ጠብቀው በኃላፊነት በማሽከርከር የመንገደኞችን ህይወት ከትራፊክ አደጋ መታደግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም