በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ሽያጭ የሚተዳደሩ አርብቶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል

168

ጥር 15/2014/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት የገበያ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ በማሳደሩ ምክንያት ከብቶቻቸውን በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው በዞኑ ተልተሌ ወረዳ የሚገኙ አርብቶ አደሮች ገለጹ።

ከዚህ ቀደም ከ30 እስከ 40 ሺህ ይሸጡ የነበሩ የቀንድ ከብቶች አሁን ላይ በድርቁ ምክንያት በ1 ሺህ ብርና ከዚህም በታች መሸጥ ግድ ብሎናል ብለዋል።

እንስሳቱ የሚሸጡበት ዋጋ ከሸቀጦችና ሌሎች ፍጆታዎች ዋጋ ጋር ባለመመጣጠኑ በኑሯቸው ላይ ችግር መፍጠሩንም አንስተዋል።

እንስሳቱን ድርቁ ከሚገድላቸው መሸጥን አማራጭ በማድረጋቸው በተደጋጋሚ ወደ ገበያ እንደሚያመላልሱ ገልጸው በርካታ እንስሳት በጉዞ ወቅት የሚሞቱባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተልተሌ ወረዳ የአደጋ ስጋት ጽህፈት ቤት ሃላፊ እና የድርቁ ታክስ ፎርስ ኮሚቴ አባል አቶ ሙሉ ዴንጌ የተከሰተው ድርቅ የአርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ በእጅጉ ማዛባቱን ገልጸዋል።

በርካታ የአርብቶ አደሩ እንስሳት በደርቁ ሳቢያ በመሞታቸውን ገልጸው ቀሪዎቹም አስቸኳይ ድጋፍ ካላገኙ በሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወረዳው ታክስ ፎርስ ኮሚቴም የእንስሳትን ሞት ማስቆም ባለመቻሉ አሁን ላይ ትኩረቱን የሰው ሕይወት ማዳን ላይ አድርጓል ነው ያሉት።

በአካባቢው ሰሞኑን የጣለው ከባድ ዝናብም በድርቁ ተጎድተው የነበሩ ከዘጠኝ ሺህ በላይ እንስሳትን በአንድ ቀን መግደሉንም አመልክተዋል።

በርካታ አርብቶ አደሮች አሁን ላይ ከሞት የተረፉ እንስሳትን በመያዝ ወደ ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች በመሰደድ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በድርቁ ምክንያት በርካታ አርብቶ አደሮች እንስሳቶቻቸውን ሙሉ ለሙሉ በማጣታቸው አፋጣኝ ድጋፍ ይሻሉም ነው ያሉት አቶ ሙሉ።

በቦረና ዞን የክረምት እና ሃገያ እየተባለ በሚጠራው የምርት ወቅት ዝናብ ባለመዝነቡ ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ በበርካታ አርብቶ አደሮች ላይ ጉዳት አድርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም