በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ ከእንስሳት በተጨማሪ በሰው ህይወት ላይ አደጋ ደቅኗል

110

ጥር 15/2014/ኢዜአ/ በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ ከእንስሳት በተጨማሪ በሰው ህይወት ላይ አደጋ ደቅኖብናል ሲሉ የአካባቢው አርብቶ አደሮች ተናገሩ።

የተደረገላቸው ድጋፍ ከችግሩ ስፋት አኳያ በቂ ባለመሆኑ መንግስትና ህዝቡ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉላችውም ጥሪ አቅርበዋል።


በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው አርብቶ አደሮች እንደተናገሩት በድርቁ ሳቢያ በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶች፣ በግ እና ፍየሎች ሞተውባቸዋል።

በአካባቢው ከዘጠኝ ወር በላይ ዝናብ ባለመዝነቡ ከፍተኛ የእንስሳት መኖ ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰው በህይወት የተረፉ እንስሳትም አደጋ እንደተደቀነባቸው አስረድተዋል።

በአካባቢው ከዚህ ቀደም ድርቅ ያጋጥም እንደነበር አስታውሰው በዚህ ዓመት የገጠማቸው ድርቅ ግን የከፋ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአካባቢው አርብቶ አደር ዋነኛ የህይወት መሰረቱ እንስሳት መሆናቸውን ጠቅሰው ብዙ እንስሳት ስለሞቱባቸው በቀጣይ ኑሯቸው ላይ ጫናው ቀላል እንደማይሆን አስረድተዋል።

በድርቁ ሳቢያ ከ30 በላይ እንስሳት የሞተበት አርብቶ አደር መኖሩን ያስታወሱት አስተያየት ሰጭዎቹ "ድርቁ ከእንስሳት ባለፈ በሰው ህይወትም ላይ አደጋ ደቅኗል" ብለዋል።

ለአካባቢው አርብቶ አደሮች ከዚህ ቀደም የተሰጠው የእርዳታ እህል በድርቁ ከተጎዳው አርብቶ አደር ብዛት አኳያ ሲታይ በቂ አይደለም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በድጋፍ የቀረበው የከብቶች መኖም ውስን በመሆኑ ሁሉንም ማዳረስ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

የአካባቢውን ችግር ለማቃለል መንግስት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጠይቀዋል።

የተልተሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብዱባ ኮንሶ፤ በወረዳው እንደ አሁኑ የከፋ ድርቅ ተከስቶ ስለማያውቅ በእንስሳትና በሰዎች ላይ ከፍተኛ ችግር ደቅኗል ብለዋል።

ለድርቁ መባባስ እንደ ምክንያት የጠቀሱት ደግሞ በአካባቢው አጠራር "የክረምት እና የሃገያ" ወቅት ዝናብ ሳይዘንብ በመቅረቱ ነው።

በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋም ችግሩን ያባባሰው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

በድርቁ ምክንያትም እስከአሁን በወረዳው ከ14 ሺህ በላይ የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን ገልጸው ከ27 ሺህ በላይ እንስሳትም ክፉኛ ተጎድተው የሞት አደጋ ተደቅኖባቸዋል ብለዋል፡፡

በመንግስት በኩል ከዚህ ቀደም እርዳታ መደረጉን ያስታወሱት ምክትል አስተዳዳሪው የእርዳታው መጠን አነስተኛ በመሆኑ ለሁሉም ቀበሌ አለመዳረሱንም ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ሰሞኑን ከባድ ዝናብ በመጣሉ በድርቁ ክፉኛ የተጎዱ እንስሳት መሞታቸውንም አቶ አብዱባ ገልጸዋል።

በወረዳው በጣለው ዝናብ አርብቶ አደሮች ውሃ በማቆር የቀሩትን እንስሳት ህይወት ለማትረፍ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን በስፍራው የተገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ተመልክቷል።

የተልተሌ ወረዳ ከቦረና ዞን ዋና ከተማ ያአበሎ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፤ ያአበሎ ከተማ ደግሞ ከአዲስ አበባ በ564 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም