በደምበል ሐይቅ ዳርቻ የሚገኘውን 1 ሺህ 254 ሄክታር መሬት በማልማት በርካታ ጎብኝዎችን ለመሳብ እየተሰራ ነው

132

ጥር 15/2014/ኢዜአ/ በባቱ ከተማ ደምበል ሐይቅ ዳርቻ የሚገኘውን 1 ሺህ 254 ሄክታር መሬት በማልማት ሰፊ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ተናገሩ።
ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 160 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የምትገኘው የባቱ ከተማ ከኢትዮጵያ የጎብኝዎች መዳረሻ ሥፍራዎች አንዷ ናት።  

ከተማዋ 440 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለው የሚነገርለትን የደምበል ሐይቅን መሰረት አድርጋ በ1953 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገርላታል።

በሀይቁ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ደሴቶችና ልዩ የጥምቀት በዓል አከባበሯ ለጎብኝዎች የሚሆኑ የምስህብ ስፍራዎች ናቸው።

የደምበል ሐይቅን ተንተርሳ በተቆረቆረችው ከተማ ተወልዶ ያደገው ወጣት በረከት ደሴ ለኢዜአ እንደገለጸው፥ በደሴቶቹ የዛይ ማህብረሰብ እና ከ1 ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት አሉ።

በተወሰኑ ደሴቶች ደግሞ ልዩ ወፎች መኖራቸውን ያነሳው ወጣቱ ከተማዋ ከእነዚህ የመስህብ ሀብቶች ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል አብራርቷል።

ወጣቶች በመልካም እንግዳ ተቀባይነት እና የመስህብ ሀብቶችን በመንከባከብ ለቱሪዝም መጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡ የጠየቀው ወጣቱ፥ የከተማ አስተዳደሩ የመስህብ ሀብቶችን እንዲያለማና እንዲያስፋፋ ጠይቋል።

ባቱ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ከተማ መሆኗን የሚናገሩት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ናቸው፡፡

አቶ ገዛኸኝ አክለውም የከተማ አስተዳደሩ የመዳረሻ ሥፍራዎችን የማስፋፋት ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነት ለመጨመርም በከተማዋና በደምበል ሀይቅ ዳርቻ የሚገኘውን 1 ሺህ 254 ሄክታር መሬት ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው ያነሱት።

ባለሙያዎች የሀይቅ ዳርቻ ንድፍና የልማት እቅዱን እንዳጠናቀቁም በቅንጅት ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል።

በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው ከተማዋ 10 ሄክታር መሬት ለሆቴሎች ልማት ማዘጋጀቷን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም