የ'በቃ' ወይም '#NoMore' እንቅስቃሴ ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖረው የማድረግ ስራ ይከናወናል

71

አዲስ አበባ፤ ጥር 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የ'በቃ' ወይም '#NoMore' እንቅስቃሴ ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖረው የማድረግና ዓለማቀፋዊነቱን የማስፋት ስራ እንደሚከናወን ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ገለጸች።

ጋዜጠኛ ሄርሜላ አሁንም "የኢትዮጵያን እውነት መናገሬን እቀጥላለሁ" ብላለች።ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ በኢትዮጵያ የነበራትን ቆይታና በቀጣይ ልትሰራ ባቀደቻቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥታለች።

'በቃ' ወይም '#NoMore' ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት በመቃወም የተጀመረ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ አፍሪካዊያንና ጥቁር ሕዝቦች የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን በመቃወም የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እያደረጉበት ይገኛል።

በእንቅስቃሴው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በማሳተፍ ሠላማዊ ሠልፍና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻዎችን ሲያካሄዱ ቆይተዋል።

የ'በቃ' ወይም '#NoMore' እንቅስቃሴ አስተባባሪ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ እንቅስቃሴው ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖረውና አጀንዳዎችን በመቅረጽ ዓለም አቀፋዊ ይዘቱ እንዲሰፋ እንደሚደረግ ገልጻለች።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲሁም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የማሳየት ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ተግባራት እንደሚከናወኑም ተናግራለች።

የ'በቃ' ወይም '#NoMore' እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን ያደረገው ዜጎች የራሳቸውን እውነት ራሳቸው እንዲናገሩ ዕድል በመፍጠሩ እንደሆነና ይህም እንደሚቀጥል ተናግራለች።

እንቅስቃሴው የጥቂት ሰዎች ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን፣ የትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሆነም አመልክታለች።

"የተለያዩ ጫናዎችና ተጽዕኖዎች እየመጡብኝ ቢሆንም አሁንም ያመንኩበትን እውነት ከመናገር ወደኋላ አልልም" ያለችው ጋዜጠኛ ሄርሜላ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ስለ ኢትዮጵያ ካልተናገርኩኝ ማን ሊናገር ይችላል? ብላለች።

"ሰዎች በውሸት ምክንያት እየሞቱ ነው ስለዚህ አሁንም እውነቱን መናገር እቀጥላለሁ" ስትል ተናግራለች።ጋዜጠኛዋ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅ ነው የመጣሁት በቆይታዬም ብዙ ነገሮችን መማርና መረዳት ችያለሁ፤ "በኢትዮጵያ የተመለከትኩት ነገር ወደ አሜሪካ ስመለስ ለቀጣይ ስራዎቼ ያግዘኛል" ብላለች፡፡

ኢትዮጵያዊያን የራሳቸው እውነታ ፊት ለፊት ወጥተው መናገር እንደሚገባቸውና የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃንም የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽና በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክታለች።

በአንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን መመከት የሚቻለው እውነተኛውን መረጃ በማሳወቅ በመሆኑ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብላለች።

መገናኛ ብዙሃን ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ተደራሽ የሚያደርጉ ዘገባዎችን ለመስራት ሙያዊ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም