"አንድ ዳያስፖራ ለአንድ ቤተሰብ'' ንቅናቄን የተቀላቀሉ የዳያስፖራ አባላት በቅርቡ ቤተሰቦቻቸውን ይረከባሉ

57

አዲስ አበባ፣  ጥር 14/2014 (ኢዜአ) "አንድ ዳያስፖራ ለአንድ ቤተሰብ'' የሚለውን ንቅናቄ የተቀላቀሉ በርካታ የዳያስፖራ አባላት በቅርቡ የሚደግፏቸውን ቤተሰቦች እንደሚረከቡ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ዳርጓል፤ ሴቶች ሕጻናትና አዛውንት ተደፍረዋል፤ ብዙዎች ቤት ንብረታቸው ወድሟል ከቀያቸውም ተፈናቅለዋል።

ይህንን ተከትሎ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍና የማቋቋም፤ የወደሙ ንብረቶችና መሰረተ ልማቶችን መልሶ የማቋቋም ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በእነዚህ ተግባራትም ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ የዳያስፖራ አባላትና ሌሎችም የዕለት ደራሽ ምግብ፣ የቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎችን በማቅረብ እየተሳተፉ ነው።

ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ለእነዚህ ወገኖች የዕለት ደራሽ ድጋፍ ከማቅረብ ባሻገር ወደ ቀደመ ኑሯቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠርና መልሶ ማቋቋም ላይ ትኩረት ማድረግ የግድ እንደሚል ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ አገራዊ ጥሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው ከመጡ የዳያስፖራ አባላት ጋር በጉዳይ ላይ መምከሩንና የዳያስፖራ አባላቱም ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

'አንድ ሻንጣ ለወገኔ' በማለት ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ወገኖቹ የተለያዩ ድጋፎችን እያበረከተ ለሚገኘው ዳያስፖራ "አንድ ቤተሰብ ለአንድ ዳያስፖራ" የተሰኘ ንቅናቄ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

በርካታ ዳያስፖራዎችም ንቅናቄውን በአጭር ግዜ መቀላቀላቸውንና ይህንኑ ተግባር ለማከናወን በተዘጋጁት አማራጮች ምዝገባ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ የሽብር ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ያወደማቸውን መኖሪያ ቤቶችና መገልገያ ንብረቶች ለመተካት በሃላፊነት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም የዳያስፖራ አባላቱ በቅርቡ ከሚያቋቁሟቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትና ስራቸውን የሚጀምሩበት መርሃ ግብር ይካሄዳል ብለዋል።

ይህ መልካም ተሞክሮ ለዳያስፖራው ብቻ የሚተው መሆን የለበትም ያሉት ሚኒስትሯ በአገር ውስጥም አቅም ያላቸው በጎ ፈቃደኞች ንቅናቄውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ሙሉ ቤተሰብ ማቋቋም ባይችሉ እንኳን 'አንድ ልጅ ለአንድ ወገን' የሚለውን ንቅናቄ እንዲቀላቀሉ ጠይቀዋል።

ይህኛው ንቅናቄ አንድ ታዳጊ ህጻን በሃላፊነት መርዳትና ማገዝ የሚያስችል ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት የደረሰባቸውን የስነ-ልቦና ጫና ማቃለልና አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላትን ያካትታል ብለዋል።

ይህ ተግባር ለአገር ግንባታ አስተዋጽኦ ከማበርከት ባሻገር ሁሉም ዜጋ በዚህ ረገድ የሚቻለውን እንዲያደርግ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም