በማደበሪያ ግዢና ስርጭት ዙሪያ የሕግ ማዕቀፍ ሊወጣ ይገባል ተባለ

72
አዲስ አበባ  ነሀሴ 23/2010 በማደበሪያ ግዥና ስርጭት ዙሪያ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ችግር እንደተፈጠረበት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ኮርፖሬሽኑ ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ከትዕዛዝ ውጭ በ450 ሚሊዮን ብር ወጪ የገዛው ቅይጥ ማዳበሪያ መስፈርቱን የማያሟላ በመሆኑ ፈላጊ አጥቶ በመጋዘን እንደሚገኝ ገልጿል። የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው ብርሃኑ የ2010 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክተው በሰጡበት መግለጫ እንዳመለከቱት በማደበሪያ ግዥና ስርጭት ዙሪያ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ "የብክነት ችግር ተፈጥሯል"። ኮርፖሬሽኑ ከመቋቋሙ በፊት በቀድሞ የእርሻና የተፈጥሮ ሐብት ሚኒስቴር የተገዛው ቅይጥ ማዳበሪያ ፈላጊ ማጣቱን የገለጹት አቶ ከፍያለው የማዳበሪያ ግዢ ላይ ፍላጎት፣ መጠንና ስርጭት ላይ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የሕግ ማዕቀፍ መንግስት እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል። በመጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የሚገኘው ቅይጥ ማዳበሪው በመንግስት በኩል ውሳኔ እንዲሰጥበትም የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም እስከ አሁን ድረስ ውሳኔ እንዳላገኘ ተናግረዋል። የማዳበሪያው ግዢ ትዕዛዝና መስፈርት ችግር እንደነበረው የገለጹት አቶ ከፍያለው የተፈጸመው ስህተት 10 በመቶ በተቋሙ ስለሆነ ስህተቱን የፈጸሙት ግለሰቦችን ከሥራ እስከ ማሰናበት የደረሰ እርምጃ  ተወስዷል ብለዋል። 90 በመቶ የሚሆነው ስህተት የተፈጸመው ከኮፖሬሽኑ ውጭ ባሉ የአስራርና ተያያዥ ጉዳዮች እንደሆነም አስረድተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ሚሊዮን 125 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዢ እና 161 ሺህ ምርጥ ዘር ለማቀረብ ማቀዱን አቶ ከፍያለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም