ቻይና የአዲሱ ትውልድ የምርምር ውጤት የሆነ ረጅም ርቀት ሮኬት ልታስወነጭፍ ነው

98

ጥር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ቻይና የአዲሱ ትውልድ የምርምር ውጤት የሆነ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሮኬት ለማስወንጨፍ ዝግጅት ማጠናቀቋን ገለጸች፡፡

ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሮኬቱ ማርች-8 ዋይ 2 (March-8 Y2) የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን የካቲት መጨረሻ ወይም መጋቢት መጀመሪያ ላይ ለማስወንጨፍ ዝግጅት ማድረጓን ዢንዋ የዜና ምንጭ በዘገባው አስነብቧል፡፡

ተምዘግዛጊ ሮኬቱ የተሰራው በቻይና የሮኬት ቴክኖሎጂን በማበልጸግ ዘርፍ በቀዳሚነት በሚጠቀሰውና በደቡባዊ የሂናን ግዛት በሚገኘው የቻይና የመኪና ቴክኖሎጂ መገጣጠሚያ አካዳሚ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ሮኬቱ ከተገጣጠመበት ስፍራ አንድ ሳምንት ከፈጀ የባህር ጉዞ በኋላ ለመጨረሻ ዝግጅት እና ፍተሻ በቻይና ዊንቻንግ ግዛት በሚገኘው የሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከል ስለመድረሱም ተነግሯል፡፡

ቻይና ይህንን ሮኬት በተሳካ ሁኔታ የምታስወነጭፍ ከሆነ በዓመቱ የመጀመሪያ የሮኬት ማስወንጨፍ ስኬት ሆኖ እንደሚመዘገብም ተገልጿል፡፡

ተወንጫፊ ሮኬቱ ሁለት መካከለኛ ደረጃ ያላቸው መወጣጫዎች ያለውና 50 ነጥብ 3 ሜትር ርዝመት እንዲሁም 356 ቶን ክብደት ይመዝናልም ተብሏል፡፡

ሮኬቱ በጸሀይ ኦርቢት ዙሪያ ለመሽከርከር 7 መቶ ኪሎ ሜትር አልቲቲዩድ ባለው ከፍታ ላይ ለመድረስ የሚያስችለውን 5 ቶን ፈሳሽ ነዳጅ የሚጠቀም ስለመሆኑም መረጃው ጠቁሟል፡፡

የሮኬቱ ዲዛይን በመሬትም ሆነ በባህር መወንጨፍ እንዲችል ተደርጎ የተሰራ ሲሆን የቻይናን ሮኬት ወደ ጸሀይ ዙሪያ የማስወንጨፍ አቅም ላይ የሚታየውን ክፍተት እንደሚደፍን ታምኖበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም