በገደብ ከተማ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ እየተካሄደ ነው

64

ዲላ፤ ጥር 13/2014 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን ገደብ ከተማ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በተመደበ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተጨማሪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ።

በከተማዋ ከ25 ዓመት በፊት የተገነባው የውሃ አገልግሎት ተቋም አሁን ላለው የከተማዋ የህዝብ ብዛት አንጻር በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ግንባታ ማስፈለጉ ተመልክቷል።

በዚህም ነዋሪው በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ሲቸገር በመቆየቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ሲያነሳው እንደቆየ የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ  ምህረቱ ተፈሪ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ግንባታው ከተጀመረ አንድ ወር የሆነው ተጨማሪ የንጹህ መጠጥ ውሃ የፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የነዋሪውን ህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ ነው የገለጹት።

ይህም አሁን ላይ 20 በመቶ የሚሸፍነው የከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ማዳረስ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ከንቲባው እንዳሉት፤ የተጨማሪው የውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ  ሁለት የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮን፣ 1ሺህ 300 ሜትር ኪዩብ የሚይዙ ሁለት የውሃ ማጠራቀሚያዎች እንዲሁም 22 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የውሃ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታን የሚያካትት ነው።

የፕሮጀክቱ ግንባታ በተያዘለት የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከይዞታ ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት ተባባሪ እንዲሆን  አሳስበዋል።

ግንባታው የሚካሄደውም ከደቡብ ክልል፣ ከጌዴኦ ዞን እና ከከተማው አስተዳደር ድጋፍ እንዲሁም ለውሃ ግንባታ የገንዘብ ብድር ከሚያቀርበው "ባስኬት" የብድር ፕሮጀክት በተገኘ ገንዘብ እንደሆነ ተመልክቷል።

የግንባታ ሥራውን የሚያከናውነው ሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መንግስቱ ቢራጋ፤ ወደ ተግባራዊ ሥራ ከገቡ አንድ ወር እንደሆናቸው ገልጸው፣ ግንባታውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ጨርሰው ለማጠናቀቅ ተግተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ከገደብ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጌታሁን አላኬ በሰጡት አስተያየት፤ በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት ንጽህናው ባልተጠበቀ  የኩሬና ወራጅ ወንዝ ለመጠቀም በመገደድ የጤና እንከን ሲገጥማቸው እንደቆየ ተናግረዋል።

የተጀመረው የንህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀከት ሲጠናቀቅ ችግራቸውን ያቃልላል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስከሚበቃ ድረስ የበኩላቸውን  ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም አስታውቀዋል።

በከተማዋ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ በመጀመሩ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ  ወይዘሮ እቴነሽ ጽጌ ናቸው።

የፕሮጀክቱ ግንባታ የቆየ የመጠጥ ውሃ ችግራቸውን ለመፍታት በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም በመተባበር የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

50 ሺህ ያህል ህዝብ እንደሚኖርባት የሚገመተው ገደብ ከተማ ከዲላ በ78 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደምትገኝ ከከተማዋ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም