የዞኑን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ አስተዳደሩና ኅብረተሰቡ በጋራ እየሰሩ ነው

64

አዲስ አበባ ጥር 13/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለተገኘው ሠላም ዘላቂነትና ኅብረተሰቡም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ገለጸ፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻዲቅ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ባደረጉት እንቅስቃሴ በርካታ ሠብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ባደረጉት ርብርብ አሸባሪዎቹ ያሰቡትን ሳያሳኩ ለሽንፈት መዳረጋቸውን አውስተዋል።

በተለይም ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ወረራውን ቀልብሳ ወደ ልማት መመለሷን ጠቅሰዋል፡፡

አሸባሪው ህወት ሰሜን ሸዋን ለቆ እንደወጣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስና ዜጎችን የማረጋጋት ስራ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

መሰረተ ልማቶችን መልሶ ስራ ለማስጀመር ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር እንደ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ እና የስልክ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

ተፈናቃይ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው በተመለሱበት ጊዜም በየአካባቢው የዕለት ደራሽ ምግብ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

አሁን በዞኑ የተገኘውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በቀደመው ጊዜ በአመራሩና በማኅበረሰቡ ጭምር የነበሩ ድክመቶችን መገምገም እና ውይይቶችን የማካሄድ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።

በቀጣይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የጸጥታ ሃይሉን የማጠናከር፣ ለኅብረተሰቡም ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራትም እየቀጠሉ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም