ሀገራዊ ምክክር በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

87

ጥር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የሀገራዊ ምክክር በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል" ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንቷ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ማቋቋምያ አዋጅን ባለፈው ሳምንት መፈረማቸውን ነው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ያስታወቁት።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ “ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም መፈረም ኃላፊነቴ ቢሆንም የእውነተኛና አካታች ብሔራዊ ምክክርን ቁልፍነት ስለማውቅ፣ ስለሠራሁበት፣ ውጤቱንም ስላየሁ አምንበታለሁ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“እንደዚህ ያለ ምክክር በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል፣ ሃሳብን በግድ መጫንን፣ ጦር መማዘዝን፣ ሕዝብንና አገርን አደጋ ላይ መጣልና ከመሳሰሉ አደጋዎች ያድናል” ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

“የንግግር፣ የመደማመጥ፣ የመከባበር አዲስ ባህል ይፈጥራል፣ እንደ እኛ ከአውዳሚ ጦርነት ማግስት ለሚገኝ አገር ጠቀሜታው የጎላ ነው” ብለዋል።

ይህንን አገራዊ ምክክር እንዲመራና እንዲያካሂድ የሚቋቋመው ኮሚሽን አባላት ጥቆማ ሲካሄድ መቆየቱን በማንሳት፥ ለአንድ ሳምንት ከተራዘመ በኋላ ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚያበቃም ጠቁመዋል።

“ለኮሚሽነርነት የተጠቆሙ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ፣ ሴቶች መጠቆም አለባቸው፣ አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት በሴቶች ላይ ያደረሰው ሰቆቃ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

“በመቀሌ እና በደሴ መጠለያ ጣቢያዎች ያነጋገርኳቸው ሴቶች ገጽታ ይህንኑ ያረጋግጣል” ሲሉ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እነዚህ ሴቶች “ምንም እንኳን እያዘኑና እያለቀሱ ቢያነጋግሩኝም እንባቸውን ጠርገው ጥያቄ አቅርበዋልም ፣ የመፍትሄ ሃሳብም ሰጥተዋል” ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በመልዕክታቸው።

“ጦርነቱ በሴቶች ላይ ያስከተለው ሁኔታ ገና በብዙ የሚታይ ነው፤ ሴት ሰለባ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄ አካል መሆንዋ ከግንዛቤ መወሰድ አለበት” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ የሴት ኮሚሽነሮች መኖር ካላቸው አጠቃላይ ኃላፊነት ጋር የእነዚህም ሴቶች ድምጽ ይሆናሉ ሲሉ አክለዋል፡፡

በመሆኑም ፕሬዝዳንቷ በቀረው ጠባብ ጊዜ የወጡትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ሴቶችን ህብረተሰቡ እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም