የጥምቀት በዓልን ያለስጋት ማክበር በመቻላችን ደስታና ኩራት ተሰምቶናል-የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

165

ደሴ (ኢዜአ) ጥር 12/2014—ወራሪው የህወሓት ቡድን ከተማችንን ከመዝረፉና ከማውደሙ ባለፈ ያደረሰብንን የስነ ልቦና ጫና ተቋቁመን የጥምቀትን በዓል ያለስጋት ማክበር በመቻላችን ኩራት ተሰምቶናል” ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አሳምነው መርዕድ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ ፈጽሞ በንጹሃን ዜጎች ላይ ታሪክ የማይረሳው ግፍ ፈጽሟል።

ቡድኑ ዘግናኝ ግፍ ፈጽሞ የስነልቦና ጫና ለማድረስ ቢሞክርም ከተማዋ  በጀግናው የወገን ጦር ከአሸባሪው ቡድን ነፃ መውጣቷን ተናግረዋል።

“በሽብር ቡድኑ የደረሰብንን ችግር ተቋቁመን የከተራና የጥምቀት በዓላትን በከተማችን በሰላም በማክበራችን ኩራት ተሰምቶኛል” ሲሉ አክለዋል።

የሽብር ቡድኑ ለህጻናትና ለሴቶች ክብርና ምህረት የሌለው አረመኔ መሆኑን በከተማዋ ወረራ በፈጸመበት ጊዜ በተግባር ማረጋገጣቸውን የገለጹት ደግሞ  ወይዘሮ በላይነሽ ደሳለ ናቸው።

“የአሸባሪው ቡድን አባላት የጎረቤቶቻቸውን ቤትና ንብረት ከመዝረፍ ፣ በየቤቱ እየዞሩ በመሳሪያ በማስፈራራት በርካታ ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል” ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት መስዋዕት በመክፈል በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተማቸውን ከሽብር ቡድኑ ነፃ ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

“በእዚህም የተበታተነው ቤተሰብ ሁሉ ተገናኝቶ የጥምቀትን በዓልን በከተማችን በአንድነትና በአብሮነት በደስታ ማክበር ችለናል” ሲሉ ገልጸዋል።

”በሽብር ቡድኑ ተንኮልና ክፋት ከተፈናቀሉት ቤተሰቦቻችን ጋር የምንገናኝ አለመሰለንም ነበር” ያሉት ወይዘሮ በላይነሽ፣ “በፀጥታ አካላት መስዋዕትነት ዳግም ተወለደን፤ አሁን ሌላ አዲስ ተስፋ ሰንቀናል” ሲሉ ተናግረዋል።

“የጥምቀት በዓልን ከቤተሰቦቻንና ወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር በአንድነት በደመቀ ሁኔታ ልናከብር ቀርቶ ቀጣይ ህወትም ይኖረናል ብለን አላሰብንም ነበር” ያሉት ደግሞ መሪጌታ መዝገበ ቃል ያሬድ ናቸው፡፡

“በፈጣሪ እገዛ ሠራዊታችን መስዋዕት ከፍሎ ከተማችን ነፃ በመውጣቷ የጥምቀት በዓልን ተወልድን ባደግንባትና በምንወዳት የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር ከተማችን ደሴ በማክበራችን ደስ ብሎናል” ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ለእምነት አባቶችና ተቋማት እንኳ ክብር የሌለው፣ ከሰው ያልተፈጠረ ጨካኝ አረመኔ በመሆኑ ከባድ ጊዜ ማሳለፋቸውንም መርጌታ መዝገበ ገልጸዋል፡፡

በከተማው የከተራና የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላም መከበሩ ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።