'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የተሰኘ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ያሳተፈ የገቢ ማሰባሰቢያ ኪነ-ጥበባዊ መርሃግብር ሊካሄድ ነው

73

ጥር 12/2014/ኢዜአ/ 'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የተሰኘ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ያሳተፈ የገቢ ማሰባሰቢያ ኪነ-ጥበባዊ መርሃግብር የፊታችን ጥር 20 በብሔራዊ ቴአትር ቤት እንደሚካሄድ የመርሃግብሩ አስተባባሪዎች ተናገሩ።

በእለቱ 'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የተሰኘ የሙዚቃ ክሊፕም ይመረቃል።


የረጅም ጊዜ ጥናትና ክህሎት የሚጠይቀው የክላሲካል ወይም ረቂቅ ሙዚቃ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ እንደተጀመረ ይነገራል፤ ሞዛርትና ቤትሆቨን በዘርፉ አይሽሬ ሙዚቃ ቀማሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የረቂቅ ሙዚቃ በአፍሪካ ባዕድ ቢሆንም ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ እና እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩን እንዲሁም ታዋቂው ፒያኒስትና የሙዚቃ ቀማሪ ግርማ ይፍራሸዋን መሰል ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ጠበብት አሉ።

ሰባት የሙዚቃ አልበሞችን ያወጣው ግርማ ይፍራሸዋ ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ደግሞ በረቂቅ ሙዚቃ ዘርፍ ላይ በሰራው ሥራ የኢትዮጵያን ስም በዓለም መድረኮች ላይ አስጠርቷል።

የኢትዮጵያን ቅኝቶች ከረቂቅ ሙዚቃ ስልት ጋር በማዋደድ የሚታወቀው ግርማ፤ 'ፍቅርና ሰላም' የተሰኘው አልበሙ የቢልቦርድ ሰንጠረዥ ላይ 23ኛ ደረጃ ተቀምጦ ነበር።

አርቲስት ግርማ ይፍራሸዋ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ በካናዳ የሙዚቃ ኮንሰርቶቹን ያቀረበ በዓለምአቀፍ ሚዲያዎች አድናቆት የተቸረው፤ ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዲፕሎማ የተቀዳጀ ባለሙያ ነው።

ሙዚቀኛነትን በክራር ሥራ የጀመረው ግርማ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እና ቡልጋሪያ አገር የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ተከታትሏል፤ በእንግሊዝ እና ጀርመን አገርም ተጨማሪ ኮርሶችን ቀስሟል።

ኢትዮጵያዊያን ሙዚቃን መሥራትም፣ ማጣጣምም እንደሚወዱ የሚናገረው ግርማ ይፍራሸዋ፤ ሙዚቃም ሆነ ሌሎች የኪነ-ጥበብ ዘርፎች በኢትዮጵያ ሕልውና ትግል ሚናቸው ጉልህ እንደነበር ይናገራል።

የረጅም ጊዜ ታሪክና ባህል ያላት ኢትዮጵያ በአሁናዊ ሁኔታ ተግዳሮት እንደገጠማት የሚናገረው ግርማ፤ አገርን ለመታደግ ከእኛ ምን ይጠበቃል? በሚል ሐሳብ 'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የተሰኘ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል።

አርቲስቱ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያ የሁሉንም ሙያተኞች ድጋፍ የምትሻበት ወቅት በመሆኑ ለአገሬ ድምጽ ለመሆን የበኩሌን ለመወጣት ነው ብሏል።

በዚህም ሐሳቡን ለገጣሚ ፍሬዘር አድማሱ በማጋራት 50 የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ 'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የተሰኘ የሙዚቃ ክሊፕ ማዘጋጀቱን ይናገራል።

ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በብሔራዊ ቴአትር 'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የተሰኘ የሙዚቃ፣ የታሪክ፣ የስነ- ጽሑፍ፣ የተውኔት፣ የስዕል ጥበብ ሥራዎችን ያካተቱ የሙዚቃ ኪነ-ጥበባዊ ድግስ ነው ብሏል።

ከዝግጅቶቹ መካከልም በገጣሚ ፍሬዘር አድማሱ የተደረሰውን የኢትዮጵያን አሁናዊ መልክ የሚገልጽ ግጥም ወደ ሙዚቃ የተለወጠ ክሊፕ እንደሚመረቅም ተናግሯል።

በኪነ-ጥበባዊ ድግሱ የሚሳተፉ መግቢያ ዋጋው በአንድ ቲኬት 1 ሺህ ብር ሲሆን፤ በመርሃ ግብሩ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ገቢውን ለተጎዱ ወገኖች  ለማዋል መታቀዱን ገልጿል።

የኪነ-ጥበብ ዝግጅቱ ጥበብ ለአገር ያላትን አጋርነት የምታሳይበት፣ ገበሬው ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ የኪነ-ጥበብ ሰዎችም ለአገራቸው ድምጽ የሚሆኑበት እንዲሆን የታለመ መሆኑን ገልጿል።

ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱ በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ የገጠማትን አሁናዊ ፈተና በጦርነት ብቻ መቋቋም እንደማይቻል ይልቁንም ሁሉም በየሙያው የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚጠይቅበት ነው ይላል።

ከፒያኖ ተጫዋቹ ግርማ ይፍራሸዋም ቀደም ሲል በጋራ መስራታቸውን ገልጾ፤ አሁንም ኢትዮጵያን እንደ አገር፣ እንደ አፍሪካ፣ እንደ ዓለም ያላትን ከፍታ ማሳየትና ታሪኳን በጥበብ ቋንቋ ማጉላት የሚያስችል ነው ብሏል።

'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' መርሃግብር መነሻውም ሰፊና ጥልቅ መልእክት የሚተላለፍበት መድረክ በማዘጋጀት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችም የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ስለመሆኑም ገልጿል።

የ'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' ዝግጅት ሌሎች ሙያ ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ ይህን ፈለግ በመከተል በተሰማሩበት ሙያ የአገር ድምጽ እንዲሆኑና ወገንን እንዲረዱ ለማበረታታትም እንደሆነ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎችም በኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች እየተዝናኑ ወገኖችን ለመደገፍ መርሃግብሩን እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም