ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ውጤት ማግኘታቸውን የባምባሲ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ

92
አሶሳ ነሀሴ 23/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ውጤት በማግኘታቸው ስራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የባምባሲ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ ከነዋሪዎች መካከል አቶ ሳዳት ነስር ለኢዜአ እንዳስታወቁት ባከናወኑት የተጠናከረ የተፋሰስ ልማትና ችግኝ ተከላ የተራቆቱ አካባቢዎች አገግመዋል፡፡ እየጠፋ የነበረው የአካባቢው የቀርከሃ ደንም መልሶ መልማቱንም አስረድተዋል፡፡ “ ለአካባቢያችን እኛ ተቆርቋሪ ካልሆን ማንም ሊጠብቅልን አይችልም' ያሉት አስተያየት ሰጪው 'ያለማነውን ደን ከእርሻ ማሳችን እኩል ነው የምንከባከበው” ብለዋል፡፡ “አሁን የእርሻ ሥራ ያለ አካባቢ ጥበቃ ዋጋ እንደሌለው ተረድተናል” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋጡማ ረመዳን ናቸው፡፡ ባገኙት ውጤት በመነሳሳት የተፋሰስ ልማትና ችግኝ ተከላን ዘንድሮም አጠናክረው መቀጠላቸውን አስተያት ሰጪ አርሶ አደሮቹ አመልክተዋል፡፡ አርሶ አደር አህመድ ሙሳ በበኩላቸው በቀበሌያቸው የተለያዩ አካባቢዎች በክትትልና እንክብካቤ ማነስ የተተከሉ ችግኞች  ሳያድጉ የህብረተሰቡ ጉልበት ባክኖ መቅረቱን ገልፀዋል፡፡ አሁንም ችግኞቹን የተከሉባቸው ሥፍራዎች በአካባቢ የሚገኙ ስደተኞች መተላለፊያ በመሆኑ  ችግኞቹ እንዳይጎዱ መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የባምባሲ ወረዳ አካባቢ ደንና መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልማድ መርቀኒ ስደተኞች በሚገኙበት አካባቢ የተተከሉ ችግኞችን በተመለከተ ከስደተኞችና ስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የአሶሳ ማስተባበሪያ ጋር በመነጋገር እንደሚፈቱ አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የሥነ-ህዝብ ባለሙያ አቶ አስፋው ታደለ ተፈጥሮና የሰው ህይወት የተሳሳረ መሆኑን ገልጸው አካባቢን መንከባከብ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ አካባቢ ደንና መሬት አስተዳደር የደን ልማት ጥበቃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ደሳለኝ በማርና እጣን ምርት እንዲሁም ከብት ማድለብ ማህበራት የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የተከናወነባቸውን ቦታዎች ከልለው በመንከባከብ በዘላቂነት እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በክልሉ በዘንድሮው ክረምት እስካሁን 10 ሺህ ሄክታር የተራቆተ መሬት ላይ 25 ሚሊዮን ያህል ችግኝ መተከሉን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም