በዓላቱ ከህዝቡና ከዳያስፖራው ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ለመምከር መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል

66

ጎንደር ፤ ጥር 12/ 2014(ኢዜአ)የዘንድሮ የከተራና የጥምቀት በዓላት የአማራ ክልል አመራር ከሕዝቡና ከዲያስፖራው ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ለመምከር መልካም አጋጣሚ መፍጠራቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ በዓላቱን ምክንያት በማድረግ ከመላው ዓለም የመጡ ዳያስፖራዎችንና  እንግዶችን ተቀብላ አስተናግዳለች።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተለይ ከዳያስፖራው ጋር ምሽቱን ጭምር እየተገናኙ በሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ፣በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትን መልሶ በመገንባትና ኢንቨስትመንትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የቢሮ ሃላፊው አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመከቱት፤ በዓላቱ በክልላዊና ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከህዝቡና ከዲያስፖራው ጋር ለመምከር መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።

በዚህም የክልሉ ህዝብ ያሉበትን ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች በመገምገም ችግሮች የሚፈቱበትን ሁኔታ ከመዘየድ ባሻገር በየድርሻቸው ቀጣይ ተልዕኮ ወስደውበታል ብለዋል።

በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራዎች  በመምጣታቸው  የክልሉን ኢኮኖሚና ቱሪዝም ለማነቃቃት እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚወሰድ ሃላፊው ተናግረዋል።

በተጨማሪም የዲያስፖራ አባላትም በሚፈልጉት የኢንቨስትመንት ዘርፍና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አሻራቸውን የሚያሳርፉበት ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ዲያስፖራዎች ሲመለሱም የሀገራቸው አምባሳደር የሚያደርጋቸው ግንዛቤ እንዲይዙ መደረጉንም ገልጸዋል።

ወጣቶች፣ ሌላውም ማህበረሰብና የጸጥታ ሃይሉ ተቀናጅተውና ተናበው በመሥራታቸው በክልሉ በዓላቱ በሰላምና በድምቀት መከበራቸውን ነው አቶ ግዛቸው ያስታወቁት።

በአማራ ክልል በቀጣይ የግዮንና የአገው የፈረሰኞች ማህበር ዓመታዊ በዓላት  እንደሚከበሩም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም