የታዋቂው አርቲስት የኑሆ ጎበና የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

82

አዳማ፤ ጥር 12/2014( አዜአ) የታዋቂው አርቲስት ኑሆ ጎበና የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተፈፀመ።

አርቲስት ኑሆ ከአባቱ አቶ መሃመድ ጎበና እና ከእናቱ ወይዘሮ ፋጡማ አደም በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ቀፊራ ገንደጋራ  አካባቢ ተወለደ፡፡

አርቲስቱ የአፍረንቀሎ የሙዚቃ ባንድ አባል በመሆን በ1960  አካባቢ ወደ ሙዚቃው ዓለም እንደተቀላቀለ የህይወት ታሪኩ ያመለክታል።

ከ10 በላይ ሙሉ አልበሞችና ከ200 በላይ ጠዓመ ዜማዎችን በአፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛና አረብኛ  ሰርቶ ለህዝብ አቅርቧል።

በቀብር ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ውይዘሮ ሰዓዳ አብዱረሃም እንደገለጹት፤ ኑሆ ጎበና፤ የኦሮሞ ህዝብ ዛሬ ለተጎናፀፈው ነፃነት መነሻ የሆኑ ጥያቄዎችን በጥበብ ስራዎቹ ነቅሶ በማውጣት ለህዝብ ያኖረ አንጋፋ አርቲስት ነበር።

አርቲስቱ ለህዝብ የኖረ አንጋፋ የጥበብ ሰው ከመሆኑም ባለፈ በአፋን ኦሮሞ የኪነ ጥበብ ዘርፍ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው ብለዋል።

በተለይ የኦሮሞ ህዝብ በጨቋኞቹ ሥርዓቶች አገዛዝ ሲደርስበት የነበረውን ግፍ በአንድነት እንዲታገል በኪነ ጥበብ ሙያው የጎላ ሚና መጫወቱንም ጠቅሰዋል።

በወቅቱ አገዛዝ በደረሰበት ጫና በስደት ላይ  ሆኖ የኦሮሞን ህዝብ አንድ ሆኖ ጭቆናን እንዲታገል ማህበረሰቡን  በማንቃት ከፍተኛ ሚና የተጫወተ እንደነበርም ተመልክቷል።

በሥነ-ሥርዓቱ እንደተብራራው፤ አርቲስቱ በቀደምት ጀግኖች የተጀመረው የእኩልነት፣ የፍትህና የነፃነት ትግል ግቡን እንዲመታ ሚናውን የተወጣ አንጋፋ  የህዝብ ልጅ ነበር።

ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ74 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ተወዳጁ አርቲስት ኑሆ ጎበና ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ነበር።

በቀብሩ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አወሉ አብዲን ጨምሮ የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ፣ የአርቲስቱ አድናቂዎች፣ወዳጅ ዘመዶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም