አገራዊ ምክክሩ መልካቸውን እየቀያየሩ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አይነተኛ መፍትሔ ነው

107

ጥር 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ መልካቸውን እየቀያየሩ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አይነተኛ መፍትሔ መሆኑን 'ዴስቲኒ ኢትዮጵያ' ገለጸ።

የምክክር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም በሆደ ሰፊነትና ትዕግስት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብሏል።

አገራዊ ቅራኔዎችንና ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት በማሰብ መንግስት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙ ይታወቃል።

በኮሚሽኑ አስተባባሪነት በሕዝቡ መካከል ያለው የሃሳብ ልዩነት፣ አለመግባባትና ተቃርኖ እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ ልዩነቶች በምክክሩ እንደሚረግቡ ይጠበቃል።

የአገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነትና ሂደቱ ዙሪያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቃርኖዎች በንግግር እንዲፈቱ ሲሰራ የቆየው 'ዴስቲኒ ኢትዮጵያ' ኃላፊ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማካይ በየ15 ዓመቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ይከሰታሉ።

የቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያ ሁኔታም ይህንን የሚያረጋግጥ እንደሆነም ገልጸዋል።

ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምክክር ከሁሉም በላይ የግጭትና የአለመረጋጋት ኡደት እንዲቋረጥ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ሀሳባቸውን በቀናነት ወደ ጠረጴዛ በማምጣት መመካከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ ልዩነቶችና ማንነቶች ተሰባጥረው የሚገኙባት አገር በመሆኗ አገራዊ ምክክሩ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት ስለሚችል ከፍተኛ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በሂደቱ ሁሉንም ማዳመጥ፣ የሁሉንም ፍላጎት ማካተትና ፍላጎቶች በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት ለውይይት መቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በአገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን እየተነጋገሩ፣ እየተደማመጡ ሲሄዱ ብዙ ችግሮች እየቀለሉ ይሄዳሉ ብለዋል አቶ ንጉሱ።

መሰል ምክክሮችን በማድረግ አገራዊ ፈተና የሆኑ ችግሮችን ከሃይል ይልቅ በንግግር ብቻ የመፍታት እድሎች እየሰፉ እንዲመጡ ያስችላል ብለዋል።

በየአካባቢው ያሉ ነባር የግጭት መፍቻ መንገዶች በአገራዊ ምክክሩ ውስጥ ጎልተው መታየት አለባቸው ሲሉ ምክር ለግሰዋል።

"በኢትዮጵያ ችግሮችን በሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች መንገዶች መፍታት የሚያስችሉ የቆዩና የዳበሩ ስርዓቶች ስላሉ ልንጠቀምባቸው ይገባል" ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም