በአብሮነትና መተባበር በህዝቦች የጋራ መሰረት ላይ የቆመች ጠንካራ ኢትዮጵያን የማስቀጠል ኃላፊነት አለብን

54

ጥር 12/2014/ኢዜአ/ "በአብሮነትና መተባበር በህዝቦች የጋራ መሰረት ላይ የቆመች ጠንካራ ኢትዮጵያን የማስቀጠል ኃላፊነት አለብን" ሲሉ ኢዜአ በጥምቀት በዓል አካባበር ላይ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነቱ ተከታዮች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱና ዋነኛው ነው።

በዓሉ ሲከበር ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች እንዳሉት፤ ቀደምት ኢትዮጵያዊያን የእምነት ልዩነት ሳይገድባቸው በጋራ በመቆም ነጻ አገርን ለትውልድ አሸጋግረዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ በአገር ግንባታ ላይ የበኩሏን አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የአሁኑ ትውልድ የእምነት ልዩነት ሳይገድበው የኢትዮጵያን ህልውና የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡

በማህበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሃይማኖታዊ አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ዲያቆን ኃይሌ አርአያ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤት መሆኗን አብራርተዋል፡፡

ትህትና እና አብሮነት ከጥምቀት በዓል መገለጫዎች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ተናግረው፤ ከዚህ አኳያ በፍቅር አብሮነትና መተባበር መኖር ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታ በመሆኑ በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል።

በማህበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል አገልጋይ ሃና ሽመልስ በበኩላቸው ምእምኑ ቤተክርስቲያኗ ለአገር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ አብሮነትን አጎልብቶ ለአገር ህልውና መስራት እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል፡፡

በታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ቤተ-ክርስቲያን ዋና ጸሃፊ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ጌታሁን ወልደአብ፤ ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ጸሎትና አብሮነት በመታገዝ ከችግሯ እየተላቀቀች ትገኛለች ብለዋል፡፡

በቀጣይም ይህንኑ እሴት በማስቀጠልና ኢትዮጵያን በህዝቦቿ የተባበር ክንድ በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም