በደላሎች እየታለሉ ለህገ ወጥ ስደት የሚዳረጉ ወጣቶችና ሴቶችን መታደግ እንደሚገባ ተመለከተ

125
ደብረ ብርሃን ግንቦት 9/2010 በደላሎች እየታለሉ ለህገ ወጥ ስደት የሚዳረጉ ወጣቶችና ሴቶችን ለመታደግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተመለከተ። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ቡድን ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል በሚቻልበት ላይ በደብረ ብርሃን ከተማ ከወጣቶች ጋር መክረዋል። በዚህ ወቅት በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት አቃቢ ህግ አቶ ውብሸት ብርሃኑ እንደገለጹት ህገወጥ የሰው ዝውውና ስደትን ለመከላከል በተቀናጀ አግባብ መረባረብ ይገባል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል በሰው ሀገር ለስቃይና እንግልት ብሎም ለሞት የሚጋለጡ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ጉዳዩን የሚያስተባብሩ ህገወጥ ደላሎችን ለመከላከልም በኢትዮጵያ ችግሩ ጎልቶ የሚታይባቸው 80 ወረዳዎች ተለይተው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ የተካሄደ እንደሆነም አመለክተዋል፡፡ አቃቢ ህጉ እንዳሉት እስካሁን በደቡብ ህዝቦችና በአማራ ክልል በ19 ወረዳዎች ተዘዋውረው በመወያየትና በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ግንዛቤ በመፍጠር ችግሩን ለማርገብ ጥረት ተደርጓል። አዲሱ አዋጅ በህገወጥ መንገድ ሰዎችን በሚያዟዙሩ፣ ስደተኞችን ድንበር በሚያሻግሩና በአቀባባይ ደላሎች ላይ ከ15 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እስራት፣ ሞትና እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያስቀጣ መሆኑንም አቃቤ ህጉ አብራርተዋል፡፡፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ቡድን አስተባባሪ አርቲሰት አዳፍሬ ብዙነህ በበኩላቸው ችግሩን ለመቀነስ ህብረተሰቡን በማስተማር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ "ከ30 በላይ አርቲስቶች በሀገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች በመዘዋወር የስደትን አስከፊነትና መዘዝ በቴአትር በማሳየት ህብረተሰቡ በሀገሩ ሰርቶ እንዲለወጥ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየሰራን ነው" ብለዋል፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ  ባልደረባ ወይዘሮ ባንችአምላክ ተፈሪ እንዳመለከቱት ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈም መሄድ አለብን ለሚሉ አካላት የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት በወጣው አዋጅ መስረት በህጋዊነት እንዲሄዱ እየተሰራ ነው። "በያዝነው ዓመትም 29 ሰዎች በተለያዩ ጠረፎች በህገ ወጥ ስደት ለመውጣት ሲሞክሩ ተይዘው ወደ ዞኑ ከተመለሱ በኋላ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው ወደየወረዳቸው ተልከዋል" ብለዋል። ባለፈው ዓመት በአንኮበር፣በአጣዬ ከተማና በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በህገ  ወጥ ሲያቀባብሉ የተገኙ ደላሎች ተይዘው ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም አስታውሰዋል። በምክክር መድረኩ ከተሳተፉት የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ማርታ ብርሃኑ በሰጠችው አስተያይት የቅርብ ጓደኛዋ በህገወጥ መንገድ ወደ ሳዑድ አረቢያ ስትሄድ በደረሰባት እንግልት አካል ጉዳተኛ መሆኗን አስታውሳለች፡ መንግስት በህገወጥ  ደላሎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥልና በየሰፈሩ እንውሰዳችሁ እያሉ የሚያታልሉትም አጋልጦ  ለመስጠት የድርሻዋን እንደምትወጣም ተናግራለች። "ወጣቶችን በህገ ወጥ መንገድ መሄድ እንደሌለባቸው ግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎን በአካባቢያቸው ሰርተው የሚለወጡበት የስራ መስክ በፍጥነት ማመቻቸት ይገባል" ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት አየለ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በደላሎች እየታለሉ ለህገ ወጥ ስደት የሚዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ወጣቶችና ሴቶችን ለመታደግ  ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ  የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት አመልክተዋል። በከተማው ከተወጣጡ ወጣቶች፣ሴቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ጋር በህገ ወጥ ስደት አስከፊነትና መፍትሄው ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን ስደት በሚል ርዕስ የተዘጋጀ  ቴአትርም ለእይታ ቀርቧል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም