በዋግ ኽምራ 95 የጤና ተቋማት በከፊል አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

97

ሰቆጣ፤ ጥር 12/2014 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው 95 የጤና ተቋማት የተወሰኑ ማስተካከያዎች ተደርጎላቸው በከፊል አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ አሳየ ገብረ ስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች  የጤና ተቋማት የህክምና መሳሪያዎችን  በማውደም ከአገልግሎት ውጭ አድርጓል።


የስርዓተ ምግብ ችግር ላለባቸው ህፃናት ማከሚያ የሚውለውን በንጥረ ነገር የበለፀገ  ምግብ "ፕላንፕሌት"  ጭምር ቡድኑ ዘርፎ መውሰዱን ጠቅሰዋል።

የሽብር ቡድኑ ጉዳት ያደረሰባቸውን የጤና ተቋማት አገልግሎት ለማስጀመር ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

እስካሁንም የሰቆጣ ተፈራ ሃይሉ መታሰቢያ ፣  የፅፅቃና አምደወርቅ ሆስፒታሎችን አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

እንዲሁም 22 ጤና ጣቢያዎችና 70 ጤና ኬላዎች የተወሰኑ የህክምና ቁሶች ተሟልተውላቸው በከፊል ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

ጉዳት የገጠማቸውሌሎች የጤና ተቋማት ጭምር ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ለማስጀመርም ከተባባሪ አካላት  ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም