የባህል እሴቶች ለትውልድ የማስተላለፉ ተግባር ትኩረት አልተሰጠውም

132
አዲስ አበባ ነሓሴ 23/2010 በኢትዮጵያ ያሉትን የባህል እሴቶች የማስተዋወቅና ለትውልድ የማስተላለፉ ተግባር ትኩረት እንዳልተሰጠው ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ። ይህንን ተግባር ለመፈጸም የተቋቋሙ ተቋማት ተግባራቸውን እየተወጡ አለመሆኑም ተጠቅሷል። አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ታዳጊ ወጣቶች በሌሎች አገሮች ባህል ተበርዘውና ማንነታቸውን በመርሳት ስለሚያድጉ የመከባበር፣ የመቻቻልና  ለአገር ጥቅም የመቆም ባህሉን እየጎዳው እንደሆነ ተናግረዋል። ታዳጊዎቹ ሰፋ ያለ ጊዜያቸውን በምዕራባውያን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በተለይም ጦርነት፣ አስፈሪ ነገሮችና ብልጣ ብልጥ ተግባራትን የሚያሳዩ ፕሮግራሞች ላይ በማተኮራቸው እሴቶቻችንን በተለይ ችግርን በጋራ የመፍታት ባህላችንን ጎድቶታል። ወላጆች ልጆቻቸው በስነ ምግባር ታንጸውና ባህላቸውን አውቀው እንዲያድጉ የሚያደርጉት ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን አስተያየት የሰጡን ወይዘሮ ብሩክቲ ተወልደ  ይናገራሉ። የመንግስት ተቋማት ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረትና የራስን እሴትና ባህል የሚያስተዋውቁ አገራዊ ፕሮግራሞችና መዝናኛዎች ባለመኖራቸው ህጻናትና ወጣቶች በቅርቡ በሚያገኟቸው በቴሌቪዥንና በሌሎች መዝናኛዎች ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ይገደዳሉ። የባህሉ መበረዘ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምንም እየጎዳ እንደሆነ የተናገሩት በባህል አልባሳት ሽያጭ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ወይንሸት ደረሰ የባህል አልባሳትንና ሌሎች ባህላዊ አልባሳትን የመጠቀም ልምድ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ይገልጻሉ። 'ሹፎን' በሚል ስያሜ የሚታወቀውና የባህል ቀሚስን በመተካት እየተዘወተረ የመጣው ቀሚስ የባህል አልባሳት ግብይት ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል። አባት አርበኛ ዳኛቸው ተመስገን እንደሚሉት፤ ህጻናት በስነ ምግባር የታነጹ ዜጋ ሆነው አገርና ወገናቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ የወላጆች ተቀዳሚ ስራ ነው። “ባህል ተረስቷል፣ መከባበርና መደማመጥ ቀንሷል፤ ወንድም በወንድሙ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር መፈጸም እየተበራከተ መጥቷል፤ ይህም በስነ ምግባር ተኮትኩቶ ያለማደግ ማሳያዎች ናቸው'' ብለዋል። ልጆችን በስነምግባር አንጾ ማሳደግና ባህላዊ እሴቶቻቸውን አውቀው እንዲያድጉ የማድረግ ስራ ለነገ የሚባል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንዳሉት የአገሪቱን ባህልና እሴት የሚያስተዋውቁና ትውልድን ለማነጽ የተመሰረቱ ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ማሳካት አለመቻላቸው በመንግስት በመታወቁ በቅርቡ የማሻሻያ ስራዎች ይሰራሉ። ያለውን የባህል ወረራ መከላከል የሚያስችል ሰፊ ስራ እንዳልተሰራም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ለ500 ታዳጊዎች ባህላዊ እሴቶቻቸውን እንዲያውቁና በስነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ የሚያደርግ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም