በዓሉን ስናከብር አንድነትና ሰላም እንዲጠናከር ቅድሚያ በመስጠት መሆን አለበት

143

ሚዛን፣ ጥር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር የመደማመጥ ባህልን በማጉላት ለሀገር አንድነትና ሰላም መጠናከር ቅድሚያ በመስጠት መሆን አለበት ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ተናገሩ።

በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሸካ፣ ቤንች፣ ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ህዝቅኤል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በውስጥና በውጭ ጠላቶቿ ብትፈተንም በህዝቦቿ ጠንካራ ስነ ልቦናና በፈጣሪ እርዳታ ችግሮቿን እያለፈች መጥታለች።

ሀገር በገጠማት ፈተና ዜጎች ሳይሸበሩ አንድነታቸውን ማጠናከርና ባህላቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግረው፤ የነገን ብሩህ ቀን በተስፋ ማሰብና መጠበቅ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ጥምቀት የሰላም በዓል መሆኑን የገለጹት አቡነ ህዝቅኤል፤  ሰላም ከሌለ ታቦት ማውጣትና በዓልን ማክበር ስለማይቻል ህዝቡ አንድነትና ሰላም እንዲጠናከር ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

"የህዝብን አንድነት ለመሸርሸር አቅደው የሚሰሩ ሃይሎች ዓላማ እንዳይሳካ የጥንት አባቶቻችንን የመደማመጥና የመከባበር ባህል በማዳበር ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል" ሲሉም አክለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የባህል፣ የትምህርትና ሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ይዘቱ ሳይበረዝ ጠብቆ ማቆየት የሁሉንም አስተዋጽኦ እንደሚጠይቅ አስታውሰው፣ ሁሉም በእኔነት ስሜት ሊጠብቀውና ሊንከባከበው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም