ወጣቱ ትውልድ ማህበራዊ ሚዲያን ለአገር ግንባታና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሊያውለው ይገባል -- አስተያየት ሰጪዎች

115
አክሱም ነሀሴ 23/2010 ወጣቱ ትውልድ ማህበራዊ ሚዲያን ለአገር ግንባታና  ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሊያውለው እንደሚገባ  የአክሱም ከተማ ወጣቶችና  መምህራን ተናገሩ። አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት  በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች አብዛኞቹ ከእውነት የራቁ በመሆናቸው ካለው የተጠቃሚ ብዛት አንፃር ጉዳት የማድረስ አቅማቸው ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪ  ወጣት አለም ልኡል እንደተናገረው  ማህበራዊ ሚዲያ በአግባቡ ከተጠቀምንበት  በርካታ እውቀቶች፣ ገንቢ ሀሰቦችና አዝናኝ መልእክቶች ይገኝበታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ከእውነት የራቁና የሚያደናግሩ መረጃዎች የሚሰራጩበት በመሆኑ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ’’ ዘወትር የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ነኝ፣ የምለቃቸው መረጃዎችም ትክክለኛ እና ከነምንጮቻቸው በማጣራት ነው ’’ በማለት የራሱን ተሞክሮ ተናግሯል፡፡ ''ወጣቱ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥና ትክክለኛውን በማሳየት አስተዋይ ሊሆን ይገባል'' ያለው ወጣት አለም ሚዲያውን ለማህበራዊ ለውጥና  ለመልካም ነገር ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል። ''ከቅርብ አመታት ወዲህ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ  የተሳሳቱ መረጃዎች ወጣቱን በማደናገር ትልቅ ተጽእኖ ፈጥረዋል'' ያለው ደግሞ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ወጣት ደሳለው ወልደገብረኤል ነው፡፡ ''ወጣቱ  በተሳሳተ መረጃ ከመደናገር ወጥቶ  ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት እና ትርምስ እንዲፈጠር በማሰብ በማህበራዊ ሚዲያ ያልሆነ መረጃ የሚለቁ ዜጎችን በመከታተል መታገል ይገባዋል'' ብለዋል፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ ለሀገራዊና ለጋራ ጥቅም ማዋል የሚቻለው መንግስት ጣልቃ በመግባት ሳይሆን ማህበረሰቡ ራሱ አጠቃቀሙን ሲያስተካክልና የአስተሳሰብ ለውጥ ሲያመጣ መሆኑን ገልጿል፡፡ ''የፌዴራል እና የክልል ሚዲያዎችም ለህብረተሰቡ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ በፍጥነት ሊያደርሱ ይገባል'' ብለዋል፡፡ ''ማህበራዊ ሚዲያ የምንጠቀም ወጣቶች ማህበራዊ ኃላፊነት ሊሰማን ይገባል'' ያሉት ደግሞ በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የውቅሮ ከተማ ነዋሪ መምህር ንጉሰ ደስታ ናቸው። በተለይ በአሁኑ ጊዜ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ ተጠምዶ እንደሚውል የገለጹት መምህር ነጉሰ  የአጠቃቀሙን ጊዜውን በማሻሻል ቁም ነገር ጨብጦ አስተሳሰቡ የሚያሳድግበት የአጠቃቀም ዘዴ ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር አስፋው ደገፋው  በበኩላቸው ''በአሁኑ ወቅት  ማህበራዊ ሚዲያ የስነ ልቦና ጦርነት የሚካሄድበት አውድ እየሆነ ነው'' ብለዋል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ስሜታዊነትን የሚታይባቸው እና የጥላቻ ንግግሮች በስፋት የሚተላለፍበት መሆኑን  ገልጸዋል፡፡ የዚሁ መፍትሄ ደግሞ ከማህበራዊ ሚዲያ  መራቅ ሳይሆን ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ፣ ልማት ለማፋጠን እና ሰላም ለማስፈን በሚደረጉት ውይይቶች በማትኮር ኃላፊነት መወጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የመንግስትና የግል ሚዲያዎችም ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ በማቅረብ  ሀገራዊ ኃፊነታቸው መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም