የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው

69

አምቦ ጥር 10/2014 (ኢዜአ) --- የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ በየደረጃው ካሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው በመስራት የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ መሆኑን ገለጹ።

በአምቦ ከተማ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የሠላምና የልማት ኮንፈረንስ ትናንት ተካሂዷል።

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ማንደፍሮ ቀጄላ እንዳሉት የአካባቢውን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላምና ልማት ኃይሎችን እኩይ ተግባር ለመመከት ሌት ተቀን እየሰሩ ናቸው፡፡

የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ ስለሰላም በመምከርና በማወያየት ለዘላቂ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

አንድነታቸውን በማጠናከር የከተማዋና የነዋሪዎቿ ሠላም የተረጋገጠ እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ የሀገር ሽማግሌ አቶ ባይሳ ፈዬራ ናቸው፡፡

ከሌሎች የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ኅብረተሰቡን በሰላም ጉዳይ የማወያየት ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውንና  በዚህም ውጤታማ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ማናየሽ ተስፋዬ በበኩላቸው ሰላምን ለማረጋገጥና ልማትን ለማስቀጠል በየቀበሌያቸው ህዘብ የማወያየት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ሰላም የሚጠብቀው በመንግሥት ብቻ አይደለም አካባቢያችንን ተባብረን የመጠበቅ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን" ብለዋል፡፡

ቄስ መላከአብ መንግሥቱ እና ሃጂ ማሃመድ አህሙድ በሰጡት አስተያየት የከተማቸውን ሠላም አስተማማኝ ለማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣት ቢሊሱማ ሞቲ እንዳለው በየደረጃው ካለው የፀጥታ ኃይል ጋርና ከኅብረተሰቡ ጋር ተባብሮ በመስራት በከተማዋ አስተማማኝ ሰለም እንዲሰፍንና ልማት እንዲፋጠን የድርሻ እየተወጣ ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሀጫሉ ገመቹ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ እያደረጉት ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው የሸኔ ቡድን የሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ህብረተሰቡ ሳይደናገር አንድነቱን አጠናክሮ የሽብር ቡድኑን እኩይ እንቅስቃሴ እንዲያመክን አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም