የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ በአዘዞ የስደተኞች መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

64

ጥር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ(ኢክናስ) በጎንደር ከተማ አዘዞ የስደተኞች መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ያደረጉት የኢክናስ የቶሮንቶና ሀምሊተን ቻፕተሮች ከፈውስ በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባባር እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ጸሐፊ ሲስተር ሀና መንግስቱ ድጋፉ የተደረገው በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በጎንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ ቀበሮ ሜዳ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ባለው የስደተኞች መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በመጠለያው ለሚገኙ ተፈናቃዮች 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ዱቄት ፣መኮሮኒ፣ የሕጻናት ወተት፣ዘይት፣አልሚ ምግቦች፣መድሐኒቶችና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።

የኢክናስ የቶሮንቶና ሀምሊተን ቻፕተሮች ከፈውስ በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመሆን ድጋፉን እንደተደረገም ተናግረዋል።

በቅርቡ ኢክናስ በአማራና አፋር ክልል አሸባሪው ሕወሓት በፈጸመው ወረራ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎችና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎችንና የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም ነው ሲስተር ሀና ያስረዱት።

በሌላ በኩል የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ የቶሮንቶ ቻፕተር ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጎንደር ቅርንጫፍ ጋር በመሆን ያዘጋጀው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ከነገ በስቲያ በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድም ነው የገለጹት።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢክናስ አመራሮችና አባላት እንደሚሳተፉና የሚለገሰው ደም ማንኛውም ደም ለሚያስፈልገው ሰው እንደሚውል አመልክተዋል።

የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ከተቋቋመበት ህዳር ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለወቅታዊ አገራዊ ጥሪ እና የልማት ፕሮጀክቶች 5 ሚሊዮን የሚጠጋ የካናዳ ዶላር በገንዘብና በአይነት ድጋፍ አድርጓል።

(የምስል ምንጭ ብርሃን ቴሌቪዥን ከቶሮንቶ)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም