የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድረግ ይገባል

85

ጥር10/2014/ኢዜአ/ የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር የተቀላጠፈ ምላሽ የሚሰጡ የአሰራር ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ከዳያስፖራው ጋር ውይይት አድርጓል።  

በመድረኩ በኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችና መልካም እድሎችን በተመለከተ ለዳያስፖራዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

በውይይቱ ላይ አስተያየት የሰጡ ዳያስፖራዎች እንዳሉት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት መሳተፍ እንዲቻል የሚያበረታቱ ነገሮች ላይ ልዩ ትኩረት መደረግ አለበት።

ከአሜሪካ አታላንታ የመጡት ወይዘሮ ፍርዶስ ሙኒር የሱፍ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ሊደረግባቸው የሚችሉና አዋጭነት ያላቸው በርካታ ዘርፎች እንዳሉ ገልጸዋል።

እርሳቸውም የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ ለራሳቸውና ለአገራቸው አስተዋፅኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።  

የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር የተቀላጠፈ ምላሽ የሚሰጡ የአሰራር ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።

ከአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የመጡት አቶ ዳኛቸው ፍሰሃ፤ በተለያዩ የዓለም አገራት የገንዘብ አቅም ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ስላሉ ለአገር ልማትና እድገት በማሰብ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ጭምር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለብን ብለዋል።

በሂደቱ የሚያጋጥሙ የቢሮክራሲና መልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት በዋነኝነት የመንግስት ግዴታ ቢሆንም የሁላችንም ሚና መኖር አለበት ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ዳያስፖራዎች በሚመርጡት የንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ላይ ለመሰማራት ሲመጡ በመንግስት ድጋፍና ማበረታቻዎች እንዲሁም ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ ብለዋል።

ለኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች በአንድ ሌሊት የሚፈቱ ባለመሆናቸው በሂደት በጋራ እየፈታናቸው እንሄዳለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም