በአሸባሪው የህወሀት ቡድን ዝርፊያና ውድመት የደረሰበት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ ተመለሰ

69

ጥር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሀት ቡድን ዝርፊያና ውድመት የደረሰበት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በከፍተኛ ርብርብ ወደ ስራ መመለሱን የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ሰኢድ ገለጹ።

ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲሰጥ ታስቦ በ93 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላለፉት አመታት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የራሱን ድርሻ ሲወጣ የነበረ ፓርክ ሲሆን በወራሪው እና ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

ስራ አስኪያጁ አቶ አህመድ እንደገለፁት ሁሉም የሚመለከተው የመንግስት እና የህብረተሰብ አካል በእልህ እና በቁጭት በመስራት ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ተሟልተው እና መሰረተ ልማቶች ተጠግነው ፓርኩ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

በፓርኩ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለማሳለጥም በአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ስር የሚገኙ እንደ ባንክ፣ ጉምሩክ እና ሌሎችም ሴክተሮች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ጨምረው ገልፀዋል።

ፓርኩ የደረሰበትን ከፍተኛ ጉዳት በማስተካከል በአጭር ጊዜ ወደስራ እንዲመለስ በማድረጉ ሂደት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የፓርኩ ጠንካራ ሰራተኞች፣ የባለሃብቶች ቁርጠኝነት፣ የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ድጋፍ ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እና የጸጥታ ሃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።

አሁን ላይ ወደ ስራ የገቡ የአምራች ድርጅት ሰራተኞች ወደ ማምረት ሂደት በአፋጣኝ የገቡ ሲሆን ሌሎች በሂደት ላይ የሚገኙ አምራች ድርጅቶችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ በመግባት በቅርቡ ኤክስፖርት ለመጀመር እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ ሲሆን አሁን ላይ በፓርኩ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጪ ሀገር ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም