የቀድሞው የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ችሎት ቀረቡ

76
አዲስ አበባ ነሐሴ 23/2010 የቀድሞው የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመርን ጨምሮ በወንጀል የተጠረጠሩ አራት ባለሥልጣናት ችሎት ቀረቡ፡፡ ችሎት ከቀረቡት መካከል የቀድሞ የክልሉ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ራህማ ማህድ ሀይቤ፣ የቀድሞ የክልሉ የዳያስፖራ ቢሮ ኃላፊ አብዱረዛቅ ሳኒ እና የቀድሞ የክልሉ የመስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሱልጣን መሐመድ ይገኙበታል፡፡ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ተረኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ዘርና ብሔርን ለይተው የክልሉን ወጣቶች አስታጥቀው ለበርካቶች ሞትና መፈናቀል እንዲሁም ለሃይማኖት ተቋማት ውድመት ምክንያት ሆነዋል በሚል ነው መርማሪው የፌዴራል ፓሊስ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው፡፡ ተከሳሾቹ በበኩላቸው የተለያየ የጤና እክል እንዳለባቸው በመጥቀስ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ የዋስትና ጥያቄ ይፈቀድልን ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ለሚያካሄደው ምርመራ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም  በቀረበው የዋስትና ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። አቶ አብዲ ከትናንት በስቲያ ሰኞ በአዲስ አበባ ከተማ አትላስ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል። በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም በመኖሪያ ቤታቸው  የጦር መሳሪያ መገኘቱም የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም