በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የጸደቁ አዋጆችንና የህግ ድንጋጌዎችን የያዘ መጽሃፍ ተመረቀ

137

ጥር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፍትህ ሚኒስቴር ከ1934-2013 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የጸደቁ አዋጆችንና የህግ ድንጋጌዎችን የያዘ መጽሃፍ አስመረቀ፡፡

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በመጽሐፉ ምረቃ ላይ እንዳሉት፤ ጥራዙ በአስፈጻሚውና በምክር ቤቶች በየጊዜው ጸድቀው የሚወጡ አዋጆችን አንድ ላይ አጠቃሎ ይዟል።

ይሕም በዜጎች ዘንድ የህግ ግንዛቤን በቀላሉ ለማስረጽ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

አዋጆቹ ቀደም ሲል በተበታተነ መንገድ ተቀምጠው እንደነበር አስታውሰው፤ በአንድ ጥራዝ እንዲጠቃለሉ መደረጉ በዘርፉ ጥናት ለሚያደረጉ ምሁራን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመንና የተሻሩ ህጎችን በስራ ላይ ካሉት ጋር ያላቸውን ልዩነት በቀላሉ በመለየት ይስተዋሉ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን ለማጥናት ያግዛል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ለዓመታት የወጡ ህጎች ተበታትነው መቀመጣቸው የህግ ባለሞያዎች በሚሰጡት አገልግሎት ላይ እክል ፈጥሮ መቆየቱንም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም የፍትሕ አሰጣጥ ሒደቱ ሊዛባ የሚችልበት እድል እንደነበር ጠቅሰው፤ ጥራዙ ችግሩን በመፍታት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተጻፉ ህጎች መመራት ከጀመረችበት አንስቶ ከ274 በላይ አዋጆችና ከ አንድ ሺህ 200 በላይ ደንብ መጽደቃቸውን የሚናገሩት ደግሞ በፍትህ ሚኒስቴር የህግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ስር አቃቤ ህግ የሆኑት አቶ ሰለሞን ጌታቸው ናቸው፡፡

በርካታ የህግ ማእቀፎች በተገቢው መንገድ መሰነድ ደግሞ የፍትህ ስርዓቱን ለማዘመንና ተፈጻሚነታቸውን ለመከታተል የጎላ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

ኀብረተሰቡ በስራ ላይ ያሉና የተሻሩ ህጎችን በትክክል ተገንዝቦ መብቱን እንዲጠይቅ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የህግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር በላይሁን ይርጋ በበኩላቸው የህግ ማሰባሰብና ማጠቃለል ስራዎች ህጎቹ በወጡበት ዓመትና ባላቸው ይዘት ማደራጀትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ለምረቃ የበቃው መጽሃፍም በዚህ መልኩ የተደራጀ መሆኑን ጠቅሰው፤ መጽሃፉ የህግ እውቀት የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጭምር በቀላል እንዲረዱት በሚያስችል አቀራረብ መሰናዳቱን ተናግረዋል፡፡

ህጎችን በወጡበት ዓመትና ባህሪ ማደራጀት እንደ አገር የሚስተዋለውን የመረጃ አያያዝ ጉድለት በመቅረፍ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

አሁን በስራ ላይ ያሉ ህጎች ወደ ፊት እየተሻሩ አለያም እየተሻሻሉ መሄዳቸው የግድ በመሆኑ የጥራዙ ይዘት በየጊዜው እንደሚታደስም ተናግረዋል፡፡

በዛሬ እለት ለምረቃ የበቃው ጥራዝ በስምንት ቅጽና እና በ29 ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 7 ሺህ 224 ገጾች አሉት፡፡ ጥራዙ በኦንላይን አማራጭ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም