የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ ህዝበ ክርስቲያኑ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል

127

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2014( ኢዜአ) የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ ህዝበ ክርስቲያኑ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጥሪ አቀረበች።

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩ ዓብይ በዓላት መካከል አንዱ ነው።

በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ፣ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ታላቅ በዓል በመሆኑም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል።

በኢትዮጵያም በድምቀት የሚከበር ሲሆን፤ አከባበሩ ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን የሚስብ ጭምር በመሆኑ በየዓመቱ በርካታ ቱሪስቶች ወደ አገር ቤት ይጎርፋሉ።

የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል እንደ ወትሮው ሁሉ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዝግጅት ማድረጓን በቤተ ክርስቲያኗ የብፁዕ ወ ቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ገልጸዋል።

በርካታ ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በዓሉን ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ደማቅ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡

ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑም ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በየዓመቱ በበዓሉ ላይ ለመታደም በርካታ ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሲሆን ይህም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦውም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በዓሉን በፍቅር፣ በአንድነት እና በህብረት የሚያከብሩት በመሆኑም በህዝቦች መካከል ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።

የዓለም አቀፍ ቅርስ ጭምር የሆነውን ይህ በዓል ህዝበ ክርስቲያኑ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ እና በተረጋጋ ሁኔታ ማክበር እንደሚጠበቅበትም ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ገልጸዋል።

በተለይ ወጣቶች ሰላምን በማስጠበቅ፣ ስነ-ስርአት በማስያዝና በማስተባበር ከዚህ ቀደም የሚያሳዩትን በጎ ተግባር አሁንም መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ጥንት አባቶች በዓሉ ሐይማኖታዊ ስርአቱንና ትውፊቱን ሳይለቅ ጠብቀው ማቆየታቸውን ጠቅሰው፤የአሁኑ ትውልድም በዓሉ ሐይማኖታዊ ስርአቱን፣ 'ዶግማና ቀኖናውን' ጠብቆ እንዲከበር እና ለትውልዱ እንዲተላለፍ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

የጥምቀት ክብረ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት በ2012 ዓ.ም መመዝገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም