ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሙሉቀን ተስፋው በባህር ዳር አቀባበል ተደረገለት

59
ባህር ዳር ነሃሴ 23/2010 ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሙሉቀን ተስፋው ባህር ዳር ከተማ ሲገባ በአካባቢዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደረገለት። ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሙሉቀን ተስፋው በአቀባበል ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገረው የአማራ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ሆኖ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ ታፍሮና ተከብሮ እንድትቆይ ያደረገ ነው፡፡ ሆኖም በተሳተና ለፖለቲካ ጥቅም ብቻ ሲባል ማንነቱን መሰረት ተደርጎ ለዓመታት ሲንገላታና ሲሰደድ ኑሯል። " ዛሬ በማንነቴ አልሳደድ ብሎ ሲደራጅና ተገቢ የሆነ ጥያቄ ሲያቀርብ ኢትዮጵያዊነትን መጻረር እንደሆነ ተደርጎ ሊተረጎም አይገባውም" ብሏል። አማራ መለያው  ዴሞክራሲ ብቻ መሆኑን አውቆ የአማራ ወጣት በክልሉ እና በሀገሩ ዴሞክራሲ  እንዲሰፍን አርአያ መሆኑን ተገንዝቦ ሊሰራ እንደሚገባ ጋዜጠኛና አክቲቪስትና ሙሉቀን አመልክቷል። የአማራ ህዝብ ወደፊትም በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተና  ዴሞክራሲን መሰረት ያደረገ መሰረታዊ ጥያቄዎች ይዞ  ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሙሉቀን ወደ ሀገሩ የመጣውም  የተጀመረውን የለውጥ ስራ የሚደግፍ የአማራው ሃብት የሆነ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ለማቋቋም በጉዳዩ ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያየት መሆኑን ተናግሯል፡፡ እያንዳንዱ ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን አስተዋጾ እንዲያበረክት ለማድረግ  እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ የአማራን ህዝብ ማንነቱን በማስከበር መብትና ጥቅሙ እንዲረጋገጥለት ዴሞክራሲን በሚያጎለብት መንገድ ተደራጅቶ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ  የአማራ ብሄር ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ናቸው። በአሁኑ ወቅት አማራን ተገቢ ያልሆነና ማንነቱን የማይወክል ስም እየተሰጠው እንደሆነ ጠቁመው፤ "ይህም የአማራን መደራጀት በማይወክሉ አካላት የሚደረገ ቅስቀሳ ነው" ብለዋል። የአማራ ማንነት በዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲጎለብት ፣ መብቱና ጥቅሙ እንዲረጋገጥ ወጣቱ በምክንያት ላይ ተመስርቶ እየተቀጣጠለ የመጣውን ትግል ዳር ማድረሰ እንደሚገባውም አሰስበዋል። ለአክቲቪስቱ ሙሉቀን ተስፋውና ለአማራ ልሳን ፀሐፊዎች የባህር ዳር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ትናንት ማምሻውን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም