የጅማ ከተማ አስተዳደር ለ28 የመኖሪያ ቤት ማህበራት መሬት አስረከበ

145

ጅማ፣ ጥር 8፣ 2014 ኢዜአ) የጅማ ከተማ አስተዳደር በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለተደራጁ 28 ማህበራት ዛሬ መሬት አስረከበ።

የከተማው ከንቲባ አቶ ነጂብ አባ ራያ  በወቅቱ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለማህበራቱ ያስረከበው በሶስት ቀበሌዎች ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተዘጋጀ 10 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ነው።

በዚህም ላለፉት ሰባት ዓመታት ተደራጅተው በአሰራር ችግር ምክንያት የቤት መስሪያ መሬት ያላገኙ 629 ነዋሪዎች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የከተማው የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዶ አባ ጊዲ የመሬት ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ችግርና የቅሬታ ምንጭ እንደሆነ ገልጸዋል።

አስተዳደሩ ለረዥም ዓመታት የነዋሪዎችን መሬት ጥያቄ መመለስ ሳይቻል መቆየቱን ተናግረዋል።

ችግሩን ለማቃለል በተያዘ አቅጣጫ መሰረት ቀደም ብለው ለተደራጁ ማህበራት ቅድሚያ በመስጠት መሬቱ መከፋፈሉን አስታውቀዋል።

በቀጣይ ዙር ተደራጅተው በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች ኅብረት ሥራ ማህበራት መሬት ተዘጋጅቶ አንደሚሰጥ አቶ አብዶ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም