ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ለብሄራዊ መግባባት ሲባል የሚወሰዱ እርምጃዎችን በማስተዋል ማየት ያስፈልጋል

48

ጅማ፣ ጥር 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ለብሄራዊ መግባባት ሲባል በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችን በማስተዋል ማየት አስፈላጊ መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ።

ምሁራኑ የሀገርን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሲባል በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችን በማስተዋል በማየት ለብሄራዊ መግባባቱ አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት ከምርጫ ውስጥ መግባት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

የትኛውንም ችግር በመነጋገርና በመመካከር ለመፍታት መሞከር የሰለጠነ አካሄድ መሆኑን አመልክተው፤ ይህንኑ መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ዮናስ ሰይፉ እንዳሉት፤ መንግስት የወሰደው እርምጃ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ይጠቅማል።

በተለይም የተወሰኑ እስረኞችን ክስ የማቋረጥ ውሳኔው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣትና ለአገራዊ ምክክሩ ጥሩ መደላድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካች ምክር ቤት አባል ዶክተር አብዱሰመድ ሁሴን በበኩላቸው "ሀገር ያለችበትን ሁኔታና ያሳለፈችውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት ሁሉን አካታች የሆነ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱ ለሀገር ከፍ ያለ ጠቀሜታ ይኖረዋል" ብለዋል፡፡

በሀገራዊ ምክክር መድረኩ መሳተፍ የሚገባቸው ወገኖች ሁሉ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

ክስ የተመሰረተባቸው አንዳንድ እስረኞች መፈታታቸው ተገቢ እርምጃ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በውሳኔው ሊገኝ የሚችለውን ሀገራዊ ፋይዳ በግልጽ ማብራራት አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

በተወሰደው እርምጃ የሀገር ህልውና ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ሰላም ለመምጣት የሚደረገው ጥረትም ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ብዙ ተስፋ እንዳለው ገልጸው፤ ዜጎች የመንግስትን እርምጃ ከሀገር ጥቅምና ከብሄራዊ መግባባት አንጻር ቢመለከቱት የተሻለ እንደሆን አመልክተዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ የሀገር አንድነትንና የህዝቦች ጥቅም የሚከበርበት እንደሚሆን ምሁራኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም