አሸባሪው ህወሀት በህብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን የስነ ልቦና ጉዳት ለመጠገን እየሰራን ነው- ዩኒቨርሲቲዎችና ኢኒስቲቲዩቱ

79

እንጅባራ ጥር 8/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሀት በህብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን የስነ ልቦና ጉዳት ለመጠገን እየሰራን ነው ሲሉ እንጅባራና ወሎ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቁ።

ህብረተሰቡ ጦርነቱ ካስከተለበት የስነ ልቦና ጫና ወጥቶ ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዲመለስ ምሁራን በእውቀት እንዲያግዙ የሚያስችል የስልጠና መድረክ በእንጅባራ ከተማ ተካሄዷል።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው በመድረኩ ላይ  እንዳሉት በአሸባሪው ህወሀት የተከፈተው ጦርነት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ካደረሰው ጥፋት በተጨማሪ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ፈጥሯል።

የዩኒቨርስቲው ምሁራን ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የዘርፉ ምሁራን ጋር በመተባበር በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሥነ-አዕምሮና የሥነ-ልቦና አገልግሎት ለመስጠት እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ምሁራኑ በጥናትና ምርምር የታገዘ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው ግኝቶቹን በመቀመር ህብረተሰቡ ከደረሰበት ጉዳት ወጥቶ ወደ ቀድሞ ህይወቱ እንዲመለስ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።

ከሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ጋር በመተባበር ለተፈናቃዮች እንደየ ችግራቸው መጠን ድጋፍ መደረጉን የገለፁት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርስቲ የሥነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መንገሻ ብርቄ ናቸው።

በጦርነቱ ምክንያት በተከሰተ የሥራ ማጣት፣ የሀብት ውድመትና በቤተሰብ መለየት የአዕምሮና የሥነ-ልቦና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በርካታ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ማህበረሰቡን ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከሚመጡ ችግሮች በማውጣት መደበኛ ህይወቱን ለማስጀመር ከፍተኛና የተቀናጀ የሥነ አዕምሮ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ረዳት ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል።

የእርስ በርስ መደጋገፍ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባና ለተጎጅዎች እንደችግራቸው መጠን ተደራሽ የሆነ የአዕምሮ ህክምና ድጋፍ መስጠት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸው በጦርነቱ የሥነ-ልቦና፣ ሥነ አዕምሮና ማህበራዊ ጉዳት የደረሰበትን ህዝብ በመደገፍ ወደ ነበረበት ህይወት የመመለስ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ነው።

የህዝቡን ችግር የመቋቋም አቅም ከፍ በማድረግ ጦርነቱ ካደረሰው ስሜት ወጥቶ የዕለት ተዕለት ሥራውን እንዲተገብርና ከልማት እንዳይደናቀፍ ማስቻል ግድ የሚል መሆኑን አመልክተዋል።

የሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የሥነ-ልቦና፣ ሥነ-አዕምሮና ማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ  የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከስነ ልቦና ጫና ለማላቀቅ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል ።

ኢኒስቲትዩቱ ኮቪድና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እየሠራ ካለው ስራ በተጨማሪ በጦርነቱ ምክንያት ለሥነ- ልቦና፣ ለሥነ-አዕምሮና ለማህበራዊ ችግር የተዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ከዳባት፣ ደባርቅና መካነ-ሰላም ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች በስተቀር ሁሉም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ያስታወቁት ደግሞ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ጀምበሩ ደሴ ናቸው።

ኮሚሽኑ ህብረተሰቡን ወደ መደበኛ ህይወትና ልማት ለመመለስ የሚያቀርበው የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ምሁራን በተቀናጀ መንገድ የሥነ ልቦና፣ የስነ አዕምሮና ማህበራዊ ድጋፍ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

አሸባሪው በአማራ ክልል ከሚገኙ  ሰባት ወረዳዎች በከፈተው ጦርነት ብቻ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ተፈናቅለው እንደነበር ጠቅሰው "አሁን ላይ የስነ ልቦና ግንባታው በትብብር ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

በአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በክልሉ ጤና ቢሮና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትብብር በተዘጋጀው የስልጠና መድረክ  በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የሥነ-ልቦና፣ ሥነ አዕምሮና ማህበራዊ ዘርፍ ምሁራን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም