ለጥምቀት በዓል ሰላማዊ ክንውን ፖሊስ በቂ ዝግጅት አድርጓል

53

ጥር 8/2014/ኢዜአ/ የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ ለጥምቀት በዓል ሰላማዊ ክንውን ፖሊስ፣ ከተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲሁም ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር በውጭ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆች በተገኙበት በድምቀት የሚከበር ሲሆን በዓሉ የፀጥታ ስጋት ሳይኖር በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ለክብረ በዓሉ ሰላማዊ ሂደት ማህበረሰቡ እንዲሁም ወጣቶች አካባቢያቸውን በመጠበቅና ስርዓት በማስከበር የሚያደርጉትን የተለመደ ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮማንደር ፋሲካ ጠይቀዋል።

የጥምቀት በዓል አከባበር በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የአደባባይ በዓል በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር በግልጽና በስውር የተጠናከረ ጥበቃ መኖሩን ጠቅሰዋል።

ከከተራ ጀምሮ እስከ ጥምቀት የተጠናከረ ጥበቃ መኖሩን ተናግረው ህብረተሰቡም ሰላም በማስጠበቅ ሂደት ከፖሊስ ጋር የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት የሚከበር በዓል በመሆኑ በፖሊስ በኩል ይህንን ታሳቢ ያደረገ እቅድ ወጥቶ ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል ኮማንደር ፋሲካ።

ማህበረሰቡ በተለመደው መልኩ መረጃ ለመስጠት ሲፈልግ በነፃ የስልክ መስመር 991 እና በ0111 11 01 11 መደወል እንደሚችል ጠቁመው በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ፖሊስ ጣቢያዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የጥምቀት ክብረ በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም