በጎንደር ከተማ ''ለአሸናፊዎች እሮጣለሁ'' በሚል መሪ ቃል የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ

78

ጎንደር፣ ጥር 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ''ለአሸናፊዎች እሮጣለሁ'' በሚል መሪ ሃሳብ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉበት የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ዛሬ ተካሄደ፡፡

ውድድሩ በቀጣዩ ሳምንት በከተማዋ በታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓት የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡

መነሻውን ፕላዛ ሆቴል በማድረግ በከተማው ፒያሳ አደባባይ የተጠናቀቀው ውድድር በወንዶች ምድብ ሀብታሙ ብርሃኑ፣ አማረ ተስፉ እና በሪሁን አስማማው በቅደም ተከተል አሸንፈዋል፡፡

በሴቶች ምድብ የተደረገውን ውድድር ደግሞ ሳምራዊት ይርጋ፣ ማስተዋል ሙሃባውና ራሄል ገብረመስቀል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት አጠናቀዋል፡፡

ውድድሩን ያዘጋጀው ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ደመላሽ አበበ፤ ውድድሩ በስፖርት የተገነባ ጤናማ ህብረተሰብ በመፍጠር የስፖርት ቱሪዝምን ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ውድድሩን ከጥምቀት ጋር በማስተሳሰር የበዓሉን ድባብ ለማድመቅና ሩጫ ትኩረት የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደተዘጋጀ አስረድተዋል፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው፤ ስፖርታዊ ውድድሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንና ወዳጅነት በማጠናከር የስፖርት ቱሪዝምን ለማነቃቃት የጎላ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ ከሆኑ ቦታዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ በሆነችው ጎንደር ስፖርታዊ ውድድሮች መካሄዳቸው የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ለውድድሩ አሸናፊዎች ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም