የሻኪሶ ከተማ ነዋሪዎችና እድሮች በጉጂ ዞን በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች ድጋፍ አደረጉ

112

ነገሌ ጥር 8/2014(ኢዜአ) የሻኪሶ ከተማ ነዋሪዎችና እድሮች በጉጂ ዞን ሰባ ቦሩ ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡

የሰባ ቦሩ ወረዳ አደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሆጤሳ እንዳሉት ድጋፉ የበቆሎ ዱቄት፣ ዘይት፣ ሳሙናና የአዮዲን የምግብ ጨው ያካተተ ነው፡፡

ድጋፉ ከ350 ሺህ ብር የሚበልጥ ግምታዊ ዋጋ ያለው መሆኑን የገለጹት ሃላፊው ድጋፉ በ12 የገጠር ቀበሌዎች በድርቅ የከፋ ጉዳት ለደረሰባቸው 400 አባወራ አርብቶ አደሮች በቀዳሚነት የሚከፋፈል መሆኑን ተናግረዋል።

ድርቁ ባስከተለው ጉዳት ከ39 ሺህ በላይ አባወራ አርብቶ አደሮች ለምግብ እህል እጥረት መጋለጣቸውን የተናገሩት ሀላፊው የችግሩ አሳሳቢነት ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ በመሆኑ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ቡሌ ሆራ ዩኒቬርስቲ ህዳር 30 ቀን 2014 በወረዳው በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች 100 ኩንታል በቆሎ እንዲሁም ለእንስሳቶቻቸው 900 እስር የሳር መኖ ድጋፍ ማደረጉንም ሃላፊው አስታውሰዋል፡፡

ነዋሪዎቹን ወክለው ድጋፉን ያስረከቡት አቶ ተሰማ ሸሪፍ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት 35 እድሮችን ጨምሮ የሻኪሶ ከተማ ህዝብ ገንዘብ በማዋጣት መተባበሩን ጠቅሰዋል፡፡

"የድጋፉን ሙሉ ወጭ በመሸፈን እስከ ስፍራው ድረስ አጓጉዘን በማስረከብ የወገኖቻችንን ችግር ለመጋራት በአካል ተገኝተናል" ያሉት ተወካዩ "ወደፊትም አቅም የፈቀደውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንገባለን" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም