ዩኒቨርሲቲው በጤና መስክ ያሰለጠናቸውን 609 ተማሪዎች አስመረቀ

71

ነቀምቴ ጥር 08/2014 (ኢዜአ)--ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በጤና መስክ በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 609 ተማሪዎች አስመረቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ  በስነ ስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርሲቲው ለ16ኛ ጊዜ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በክሊኒካል ነርሲንግ፣ በፋርማሲ፣ በአዋላጅ ነርስነት፣ በህክምና ዶክተርነትና በእንስሳት ሀኪምነት የተሰጣቸውን ስልጠና በአግባቡ ያጠናቀቁ ናቸው ።

ዩኒቨርሲቲው ትላንት ካስመረቃቸው መካከል 14ቱ የሕክምና ዶክተሮችና 15ቱ የእንስሳት ሀኪሞች መሆናቸውን ጠቁመው ባጠቃላይ ምሩቃን በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

ተመራቂዎች በተመረቁበት ሙያ ሕብረተሰቡን በትጋትና በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ስለሺ ጋሩማ ትምህርት ማለቂያ ስለሌለው ምሩቃን የበለጠ እውቀትና ክህሎትን በማዳበር ሕብረተሰብን ለማገልገል ጠንክረው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በፕላዝማ ቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልእክት ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከእድሜው አንጻር በጤና መስክ በሚያካሂዳቸው ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም ሙያተኞችን በማፍራት እያከናወነ ያለው ተግባር አርአያ ያደርገዋል።

በክሊኒካል ፋርማሲ 3 ነጥብ 66 በማግኘት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ተመራቂ አያት ሙሂዲን በተማረችው የሙያ መስክ ህሙማንን በእኩልነት ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡

ሀገሪቱ በምፈልጋት ቦታ ሁሉ በሙያዋ ለማገልገል መዘጋጀቷንም ገልፃለች።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች ከ77 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከልም ከ3ሺህ በላዮቹ በጤና ዘርፍ የሰለጠኑ መሆናቸው ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም