የክልሉን ፖሊስ በዘርፉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ማበልጸግ ይገባል

62

አዳማ፣ ጥር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የክልሉን ፖሊስ በዘርፉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ለማበልጸግ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኦሮሚያ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሻፊ ሁሴን አስገነዘቡ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊስና ወታደራዊ ሳይንስ ለሁለት ዓመት በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ዛሬ አስመረቀ።

ኮሌጁ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር በፖሊስና ወታደራዊ ሳይንስ አሰልጥኖ ያስመረቃቸው ፖሊሶች ቀደም ሲል በተለያየ ሙያ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸው በሥነስርዓቱ ላይ ተገልጿዋል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ ሻፊ ሁሴን በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ የክልሉን ፖሊስ በዘርፉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ለማበልጸግ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው የቀሰሙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉ ፖሊስ አባላት ሰላምን ለማደፍረስ እኩይ ዓላማ ያነገቡ የሽብር ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለማምከን አኩሪ የጀግንነት ተጋድሎ እየፈጸሙ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ረዳት ሙሐመድ አህመድ ፖሊስ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ ቀን ከለሊት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።ነው።

የዕለቱ ተመራቂ ፖሊሶች የክልሉን ፖሊስ በሰለጠነ የሰው ኃይል ለማብቃት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተመለምለው የሰለጠኑ ናቸው።

ተመራቂዎች ሕዝባቸውን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል፣ የሲቪልና ፖሊሳዊ ሳይንስን በማቀናጀት የአስተሳሰብ አንድነት፣ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እንዲመጣ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኮሌጁ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ቶልቻ መገርሳ እንዳሉት ኮሌጁ ህዝባዊ ወገንተኝነትን የተላበሰ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ብቃት ያላው የሰለጠነ የሰው ኃይል በብዛትና በጥራት ለማፍራት እየሰራ ነው።

በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የረቀቀ የመጣውን ወንጀል ለመከላከል በዘርፉ ቴክኖሎጂ በቂ ዕውቀትና  የመጠቀም ክህሎት ባለው የሰው ኃይል የፖሊስ ሠራዊቱን ማጠናከር ማስፈለጉንም ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ በፖሊሳዊ ሳይንስ፣ ወታደራዊ ሙያና ስነ ምግባር፣ በኢንቴሌጀንስና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በሌሎች የሙያ ዘርፎች የሰለጠኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም