የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

87

ጥር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ብሔራዊ መግባባትን ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎችን አቅዶ እየሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ተናገሩ።

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ባለፉት ሦስት ዓመታት ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራትና ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ግጭቶችን ለመፍታት፣ ጉልህ ሠብዓዊ የመብት ጥሰቶችን ለማጣራት፣ የሽግግር ፍትህ ለመስጠት፣ ብሔራዊ መግባባት ለማረጋገጥ የሕዝብ አብሮነትን ለማጠናከር ሲባል ኮሚሽኑ መቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡

ይሁንና ከሚሽኑ በየጊዜው በሚያጋጥሙት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር መግባት አለመቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም በአገሪቱ የተፈጠረው ጦርነት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ኮሚሽኑ በሙሉ አቅሙ እንዳይንቀሳቀስ ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመቅረፍ የሕግ ማሻሻያ በማድረግ፣ ተገቢ አሰራሮችን በመዘርጋትና ዓለም አቀፍ የዘርፉ ልምዶችን በመቅሰም አቅም ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።  

ይህንንም ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በክልልና በዞን ደረጃ ጭምር ግጭት የመፍታትና የማርገብ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

በመላ አገሪቱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የማጣራትና የሽግግር ፍትህ መሥጠት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም በመግለጽ።  

ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆንም የብሔራዊ መግባባት ሥራ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኮሚሽን ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ተልዕኮውን ለመፈጸም እንዲያስችለው መንግሥትና ሕዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ  እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽኑ ጉልህ ሰብአዊ መብት ማጣራት፣ ግጭቶችን መፍታት፣ የሽግግር ፍትህ መስጠት፣ የህዝብ አብሮነትና አንድነት ማጠናከር እሴቶቻችን ስራ ላይ ማዋል እና ለብሔራዊና ሌሎች መግባባቶች የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልበት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም የስራ ዘመኑ ተራዝሞለት፣ የህግ ክፍተቶቹ ተቀርፈውለት፣ የሽግግር ፍትህ ለመስጠትና እርቀሰላም የማውረድ ተልዕኮውን እንዲፈጽም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

አገርን ወደ ሰላም እና የእድገት ጎዳና ለማሸጋገር የበኩሉን እንዲወጣ የመንግስት እና የህዝብ አስፈላጊ ድጋፍና ተሳትፎ እንዳይለየውም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም