ውድመት የደረሰባቸውን ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሥራ ለማስገባት የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

71

ጥር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ውድመት የደረሰባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሥራ ለማስገባት የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። 

የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ”በድህረ ግጭት ማገገሚያ ተግዳሮትና ዕድሎች" ዙሪያ ከሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሃት ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።

ከ4 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ 1 ሺህ 90 ዎቹ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጸዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ በአማራ ክልል ብቻ ቡድኑ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹን መልሶ ለማቋቋምና ወደ መማር ማስተማሩ ሥራ ለመመለስም ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በመዘጋታቸው የተነሳ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትሉ በርብርብ ፈጥነው ወደ ስራ እንዲመለሱ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና መልሶ ግንባታውን በሃላፊነት ለመተግበር በዕለቱ ስብሰባ ጠቃሚ ሀሳቦች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃብታሙ አበበ በበኩላችው የወደሙትን ዩኒቨርሲቲዎች መልሶ ለመገንባት ቅንጅታዊ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም