በጋምቤላ ከተማ ጎርፍ ጉዳት አደረሰ

210
ጋምቤላ ነሃሴ 23/2010 በጋምቤላ ከተማ ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በሰው አካልም ሆነ ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተመልክቷል፡፡ የከተማው ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኡጁሉ ኡኮዝ ለኢዜአ እንደገለጹት ጎርፉ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰው ሌሊት ለሶስት ሰዓታት ያለማቋረጥ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ነው፡፡ ፖሊስ ባካሄደው የማጣራት ስራ ከ20 በላይ ቤቶች ከውስጥ ንብረታቸው ጋር ከጥቅም ውጪ ማድረጉንና ከ300 የሚበልጡ ቤቶች ደግሞ በጎርፍ እንደተጥለቀለቁ ተናግረዋል። ፖሊስ ጉዳት በደረሰባቸውን አካባቢዎች የንብረት ጥበቃና የጠፋ ንብረት ግምት የማጣራት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ዋና ኢንስፔክሩ አመልክተዋል፡፡ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል በከተማው የቀበሌ ሶስት ነዋሪ  ሻምበል አያሌው በላይነህ በሰጡት አስተያየት የጎርፍ አደጋው እየተከሰተ ያለው የማፋሰሻ ቱቦዎች በአግባቡ ባለመሰራታቸውና  በውሃ መውረጃዎች በሚካሄድ ህገ ወጥ ግንባታዎች ነው፡፡ ቦዮቹ በቆሻሻ በመሞላታቸውና የተጀመረው የማፋሰሻ ቱቦ ግንባታ በወቅቱ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የቀበሌ አራት ነዋሪ አቶ ኡማን ኚጊዎ ናቸው። በኢትዮ ቴሌኮም የጋምቤላ ሪጅን ማናጀር አቶ አወል አብደላ በበኩላቸው " በአካባባው የውሃ ማፈሳሻ ቱቦዎች በአገባቡ ባለመሰራታቸው በተደጋጋሚ ጎርፍ ወደ ቢሮ እየገባ በኔትዎርክ እቃዎችና ሌሎች ንብረቶች ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው "ብለዋል። የሚመለከተው አካል በተደጋገሚ እየተከሰተ ያለውን የጎርፍ አደጋ ችግር በዘላቂነት የሚፈታበት ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚጠበቅበትም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል፡፡ የጋምቤላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሳይመን ቦር ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ህብረተሰቡ ለጎርፍ አደጋው መፈጠር የቱቦዎች መጥበብና ከህገ ወጥ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ የመጣ ችግር ነው ማለቱ ትክክል መሆኑን ገልጸዋል። "ማዘጋጃ ቤቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን በውሃ መውረጃ አካባቢ  የተሰሩ ህገ ወጥ ግንባታዎችን በማስነሳት ችግሩን ለማቃለል ጥረት ያደርጋል "ብለዋል። በተጨማሪም ጠባብ የሆኑ የማፋሰሻ ቱቦች ላይ ጥናት በማድረግ የማሻሻያ ስራዎች እንደሚካሄዱ ጠቁመው በአሁኑ ወቅትም የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። የኢዜአ  ሪፖርተር በስፍራው በተዘዋወረበት ወቅት  በከተማው አምስቱም ቀበሌዎች የተለያዩ መኖሪያ ቤቶች ፣የመንግስትና የግል ተቋማት በጎርፍ ተጥለቅልቀው ተመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም