ለውጭ ገበያ ከቀረበ የማዕድን ምርት 283 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

92

አዲስ አበባ፣ ጥር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የማዕድን ምርት 283 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ማዕድንና ነዳጅ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የስድስት ወር የእቅድ አፈጻጸም ከክልሎች ጋር በመሆን ዛሬ ገምግሟል።

የማዕድን ነዳጅ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በዚሁ ጊዜ የማዕድን ዘርፉ በአገራችን ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ዘርፉ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ተቋማዊ የለውጥ ሥራ የተሰራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።   

የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የማዕድን ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል አቅም መኖሩን አስረድተዋል።  

በአገሪቱ ያሉት የተፈጥሮ ጸጋዎች የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ባገናዘበና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ለመጠቀምም ትኩረት እንደሚደረግም ነው የገለጹት።  

የማዕድን ሃብት በሚገኙባቸው አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ለፓትሮል አገልግሎት የሚውሉ 20 መኪናዎች ግዢ የተፈጸመ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሚኒስቴሩ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ መሓመድ ይምር የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ስድስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ከወርቅና ከሌሎች ጌጣጌጦች ማዕድናት 283 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ መሆኑን ነው የገለጹት።

የማዕድንን ምርት በስፋት የሚጠቀሙ የኢንዱስትሪ ዘርፎችን ለይቶ የሚያጋጥማቸውን የግብዓት ችግሮች የማቃለል ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል።

ለኢንዱስትሪዎችን በተደረገው ድጋፍም  እስከ 10 ሺህ ቶን የምርት ጭማሬ ያሳዩ ፋብሪካዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት እስከ 275 ሚሊዮን ዶላር በዓመት እንደምታወጣ ተናግረው ይህንንም በአገር ውስጥ ምረት ለመተካት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ በጥራት ለማምረት ለሚችሉ ስምንት ኩባንያዎች ፋብሪካ ለመትከል የሚያስችል ፍቃድ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የማዕድን መረጃ ለሚፈልጉ አካላት የማዕድን አይነቶች፣ ክምችት፣ የመገኛ ሥፍራዎችን የመሳሰሉትን መረጃ የሚያሳይ ማዕከል ግንባታ 65 በመቶ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም